Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሕብረት ስራ ማህበራት ሚና ገበያን ለማረጋጋትና የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ…

አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕብረት ስራ ማህበራት ገበያን በማረጋጋት እና የኑሮ ውድነትን ከመቀነስ አንጻር ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ አሉ የኢትዮጵያ ሕብረት ሥራ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አቶ ጌትነት ታደሰ።

“ሕብረት ሥራ ከምርት እስከ ግብይት፤ ከአምራች እስከ ሸማች” በሚል መሪ ሐሳብ ሀገር አቀፍ የሕብረት ሥራ ሲምፖዚየም መካሄድ ጀምሯል።

ኮሚሽነሩ በዚህ ወቅት÷ የሕብረት ስራ ማህበራት በኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ ውስጥ የማይተካ ሚና በመጫወት ከተረጅነት ለመውጣት በሚደረገው እንቅስቃሴ ከፍተኛ የሆነ አቅም መፍጠር እንደሚችሉ ተናግረዋል።

የሕብረት ስራ ማህበራት የገጠር ትራንስፎርሜሽንን ዕውን በማድረግ ረገድም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አብራርተዋል።

እንዲሁም ማሕበራቱ ገበያን በማረጋጋት እና የኑሮ ውድነትን ከመቀነስ አንጻር ቁልፍ ሚና እንደሚጫወቱ አንስተው÷ ለስኬታቸው ሁሉም ርብርብ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው÷ ኮሚሽኑ እና የሕብረት ስራ ማሕበራት አደረጃጀቶች ለችግሮች መፍትሔዎችን በማቅረብ ረገድ ትልቅ ሚና እንዳላቸው አመልክተዋል።

ከተማ አስተዳደሩ የሕብረት ስራ ማሕበራት እንቅስቃሴን ለመደገፍ በልዩ ትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የሕብረት ስራ ማሕበራት በሚያከናውኗቸው ስራዎች ከፍተኛ ለውጦች እየተመዘገቡ እንደሚገኙ ገልጸው÷ አሁንም በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።

በተለይም የፋይናንስ አቅማቸውን ለማሳደግ መስራት እንደሚያስፈልግና ባንኮችም ከማህበራት ጋር በመተባበር ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ12ኛ ጊዜ የሚካሄደው የኤግዚቢሽን እና ባዛር መክፈቻ መርሐ ግብር በነገው ዕለት በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል እንደሚካሄድም ተገልጿል።

በዮናስ ጌትነት

Exit mobile version