አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ከዩናይትድ ኪንግደም የኮመንዌልዝ፣ ልማት ጉዳዮችና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢቬት ኩፐር ጋር ተወያዩ፡፡
በውይይታቸውም ሁለቱ ወገኖች የአፍሪካ ኅብረት እና ዩናይትድ ኪንግደምን አጋርነት ለማጠናከርና በህግ የሚመራ የባለብዙ ወገን የዓለም ስርዓትን ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ማህሙድ አሊ ዩሱፍ በዚሁ ወቅት፥ ዩናይትድ ኪንግደም ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን የረዥም ጊዜ አጋርነትና በዓለምአቀፍ ዲፕሎማሲ የምትጫወተውን ሚና አድንቀዋል፡፡
በተለይም ሀገሪቱ ከአፍሪካ ኅብረት አባል ሀገራት ጋር የጤና፣ የትምህርት፣ የአየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም የጸጥታና ንግድ ዘርፎችን ጨምሮ ቅድሚያ በሚሰጣቸው መስኮች ለምታደርገው ትብብር ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በተጨማሪም የአፍሪካ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከልን (አፍሪካ ሲዲሲ) የጤና አገልግሎት አቅም ለማሳደግና ለአፍሪካ ኅብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ስኬታማነት እያበረከተችው ላለው አስተዋጽኦ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሯ በበኩላቸው፥ በዓለምአቀፍ ዲፕሎማሲ እንዲሁም በቀጣናዊ ሰላምና ልማት ዙሪያ የኅብረቱን አመራር ሰጪነት አድንቀዋል፡፡
በተጨማሪም በሱዳን እና ሳህል ቀጣና ሰላምና ደህንነት ዙሪያ ትብብራቸውን ስለማጠናከር እንዲሁም ለሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የሚደረገውን ድጋፍ በተመለከተ መክረዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች የአፍሪካ ኅብረትና የዩናይትድ ኪንግደም የጋራ ከፍተኛ ስትራቴጂያዊ ስብሰባ በለንደን ለማካሄድ መስማማታቸውን ኅብረቱ አስታውቋል፡፡

