አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ እንዲሳተፉ መደረጉ ለፋይናንስ ዘርፉ አዲስ ቴክኖሎጂና ልምድን ይዞ ይመጣል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ለምክር ቤቱ አባላት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያውቸውም በፋይናንስ ዘርፉ ባለፉት ስድስት ወራት መንግስት የወለድ ማሻሻያ ማድረጉንና ባንኮች በብሔራዊ ባንክ ብቻ ያደርጉት የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ግብይት በግል እንዲያደረጉ መፈቀዱን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት ባንኮች ከግማሽ ትሪሊዮን ብር በላይ ገንዘብ አንቀሳቀሰዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በዚሁ ጊዜ ውስጥ ለባንኮች የሚደረገው የገንዘብ አቅርቦት 10 በመቶ እንዲሁም ቁጠባ 44 በመቶ ማደጉን አንስተዋል፡፡
መንግስት ያቀረበው ብድር 123 በመቶ መጨመሩን ገልጸው፥ ከዚህ ውስጥ 90 በመቶው ለግሉ ዘርፉ መቅረቡንና ይህም የግል ፋይናንስ ዘርፉ እንዲነቃቃ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
ቀደም ሲል የመንግስት ብድር በከፍተኛ ደረጃ የሚሰራጨው ለመንግስት የልማት ድርጅቶች እንደነበር አስታውሰው፥ አሁን ግን አብዛኛው የመንግስት ብድር ለግሉ ዘርፍ እንደሚቀርብ አብራርተዋል፡፡
ላለፉት 20 እና 30 ዓመታት የኢትዮጵያ ባንኮች ብቻቸውን እንዲሰሩ ተደርጓል፥ ነግር ግን በባንክ ዘርፉ የተገኘው ልምድ በበቂ ሁኔታ እያደገ አለመምጣቱን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ እንዲገቡ መደረጉ ካፒታል እና ቴክኖሎጂን በማምጣት ለፋይናንስ ዘርፉ እድገት በጎ ሚና እንደሚኖራቸው ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ባንኮች ከአጠቃላይ ኢኮኖሚው ያላቸው ድርሻ ከ5 እስከ 7 በመቶ መሆኑን ጠቁመው፥ የውጭ ባንኮች የተሳተፉባቸው የሌሎች ሀገራት ባንኮች ከፍ ያለ የኢኮኖሚ ድርሻ እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡
ለአምስት የውጭ ባንኮች በአምስት አመት ውል እና በ49 በመቶ ድርሻ በባንክ ዘርፍ እንዲገቡ ፈቃድ መሰጠቱን አስታውሰው፥ ይህም በኢትዮጵያ ባንኮች ላይ ተፅዕኖ እንደማያመጣ አስረድተዋል፡፡
የሀገር ውስጥ ባንኮች ከእቁብ ወጥተው ባንክ መሆን አለባቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በየሰፈሩ ባንክ ከመክፍት ይልቅ ካፒታልና የሰው አቅማቸውን በማሰባሰብ ትልቅ አቅም እንዲፈጥሩ አሳስበዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ

