አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሃዊና ሰላማዊ እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች የነቃ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል አለ ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ፡፡
የፓርቲው ሊቀ መንበር አብዱልቃድር አደም (ዶ/ር) እንዳሉት፥ ፓርቲው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና በክልል ም/ቤቶች በቂ ውክልና ለማግኘት የሚያስችለውን የምርጫ ስትራቴጂ አዘጋጅቷል፡፡
የምርጫ ስትራቴጂው ፓርቲው ከተፎካካሪነት ወደ መሪነት ተሸጋግሮ ጠንካራ መንግስት መመስረት እንዲችል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ነው ያሉት፡፡
ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በመጪው ጠቅላላ ምርጫ ዲሞክራሲያዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፎካከር ሰፊ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የምርጫ ጉዳዮች ኃላፊ ካሚል ሰኢድ በበኩላቸው፥ ፓርቲው በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
ፓርቲው ከተመሰረተ 7ኛ ዓመቱ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፥ ለመጪው ምርጫ የሚመራበትን ፍኖተ ካርታ የያዘ ስትራቴጂ ሰነድ ማዘጋጀቱን ነው የገለጹት፡፡
በግዛቸው ግርማዬ

