አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለመምህራን የመኖሪያ ቤት ህንፃ ግንባታ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አስጀምረዋል።
ከንቲባዋ በዚህ ወቅት የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝና በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
6 ሺሕ 194 መምህራን በ57 ማህበራት በመደራጀት በ25 በመቶ በመቆጠብ 3 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር የቆጠቡ ሲሆን÷ ቀሪውን 75 በመቶ በመንግሥት በኩል የብድር ሁኔታዎች መዘጋጀታቸውን አንስተዋል።
24 ቢሊየን ብር የሚያወጣ 40 ሔክታር የመኖሪያ ቤት ግንባታ መሬት ከተማ አስተዳደሩ በነፃ ለመምህራን ማቅረቡን ገልጸው÷ በካሳ መልክም 5 ቢሊየን ብር መከፈሉን ተናግረዋል።
ለመምህራን የሚገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ደረጃቸውን የጠበቁና የአዲስ አበባ ከተማን ውበት የሚመጥኑ መሆናቸውን አመልክተዋል።
መምህራን የቤት ባለቤት መሆናቸው የኑሮን ጫናን በማቃለል ትውልድን የማነጽ ሥራ በአግባቡ ለመከወን እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።
መምህራን ከሚያነሷቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች መካከል የቤት ጉዳይ አንዱ መሆኑን የገለጹት ከንቲባዋ÷ ከተማ አስተዳደሩም ምላሽ መስጠት የሚያስችል እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡
በግዛቸው ግርማዬ
👉ለፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎች የፋና ዲጂታል አድራሻዎችን ከአስተያየት መስጫ ሳጥን ያግኙ፡-

