አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ደቡብ አፍሪካ የአፍሪካ ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ (አፍሪኤግዚም) ተቀላቅላለች።
የሀገሪቱ ፓርላማ ደቡብ አፍሪካ የአፍሪኤግዚም ባንክ አባል እንድትሆን በፈረንጆቹ 2025 ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት የአፍሪካን ትልቁ የፋይናንስ ተቋም መቀላቀሏ ነው የተገለጸው።
ይህንን ተከትሎ የአፍሪኤግዚም ባንክ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ፕሮግራም ለመደገፍ የሚውል የ8 ቢሊየን ዶላር የብድር ስምምነት ይፋ አድርጓል፡፡
ስምምነቱ ደቡብ አፍሪካ እና ባንኩ በንግድ ዘርፍ በትብብር እንዲሰሩ መሰረት ከመጣል ባለፈ በዓለም አቀፉ የፋይናንስ መዋቅር ውስጥ አዳዲስ የንግድ አማራጮችን ለመጠቀም እድል የከፈተ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በተጨማሪም በአፍሪካ ውስጥ ያለውን የንግድና ኢንቨሰትመንት አማራጮች ለማስፋፋት እና ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሏል፡፡
እንደ ባንኩ መረጃ ደቡብ አፍሪካ በፈረንጆቹ 2024 ካደረገችው አጠቃላይ የንግድ ልውውጥ ውስጥ 19 ነጥብ 1 በመቶ የሚሆነው በአፍሪካ ሀገራት ጋር የተደረገ ነው፡፡
በአፍሪካ አንደኛ ኢኮኖሚ ያላት ደቡብ አፍሪካ የአፍሪኤግዚም ባንክ አባል መሆኗ በአሕጉሪቱ የኢንዱስትሪ ልማትን እና ቀጣናዊ የአቅርቦት ሰንሰለቶችን በማጠናከር የኢንቨስትመንት ፍሰትን ሊያሳድግ እንደሚችል ተመላክቷል፡፡
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ እንዳሉት÷ አፍሪኤግዚም ባንክ ላለፉት 30 ዓመታት በአፍሪካ ተፅዕኖ ፈጣሪ የፋይናንስ ተቋም እየሆነ መጥቷል።
ከባንኩ ጋር የተደረሰው ስምምነትም ለሀገሪቱ የንግድ ፕሮሞሽን ፕሮግራም፣ ለኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ማጠናከሪያ እንደሚውል ጠቁመዋል፡፡
የአፍሪካ ልማት ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ጆርጅ ኢሎምቢ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ደቡብ አፍሪካ የአፍሪኤግዚም ባንክ አባል መሆኗ ባንኩ በአፍሪካ ሀገራት ያለውን ኢንቨስትመንት ለማስፋፋት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
በሚኪያስ አየለ

