Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮ ኬንያ የመከላከያ የጋራ ኮሚቴ ስብሰባ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኬንያ ናይሮቢ ላለፉት ሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ እና ኬንያ የሁለትዮሽ የመከላከያ የጋራ ኮሚቴ ስብሰባ ተጠናቅቋል።

ስብሰባው የሁለቱ ሀገራት መከላከያ የመግባቢያ ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደ መደበኛ ስብሰባ ነው።

በመተማመን፣ በመከባበርና በጋራ ጥቅም መርህ ላይ የተመሰረተው የኢትዮጵያ እና የኬንያ መከላከያዎች ግንኙነት የሀገራቱን ጥቅም ከማስጠበቅ ባሻገር በቀጣናው ሰላም እና ደህንነት እንዲጠበቅ የጋራ ኃላፊነት እንዳለበት ተገልጿል።

በዚህ ረገድ ኮሚቴው ባለፈው ዓመት በሰራው ስራ ውጤታማ እንደነበረ የኢትዮጵያ መከላከያ ልዑክን የመሩት የመከላከያ የውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ ገልፀዋል።

በመድረኩ የሀገራቱን የአጋርነትና የአብሮነት ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ አጀንዳዎች ላይ ምክክር መደረጉን ጠቅሰው፥ የቀጣናው አሁናዊ ሁኔታ የሚጠይቀው የጋራ ተሳትፎ ጠንካራ ቁመና እንዲያዝ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።

የመከላከያ የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ለማጠናከር መሰራት እንዳለበት ገልጸው፥ የኢትዮጵያ መከላከያ በኃላፊነት፣ በትጋትና በውጤታማነት የድርሻውን ለመወጣት የሚያስችል የላቀ ዝግጁነት አለው ብለዋል።

የኬንያ ልዑክ መሪ የሀገሪቱ የመከላከያ ኦፕሬሽን፣ ኢንዶክትሪኔሽንና ስልጠና ኃላፊ ሜጀር ጄኔራል ሉዋሬ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ እና ኬንያ ለዘመናት የቆየ ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ትስስር አላቸው ነው ያሉት።

በንግድ፣ በኢንቨስትመንት እና በኢነርጂ ዘርፍ ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸውም ጨምረው ገልጸዋል።

የሀገራቱን የጋራ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ የሰላም እና ጸጥታ ዘርፎች የሚደረገውን ግንኙነት እና ትብብር በማጠናከር ረገድ መድረኩ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት መናገራቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል።

Exit mobile version