አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኅብረ-ብሔራዊ አንድነት ላይ የተመሰረተ የወል ትርክት ሰላምን ለማጽናትና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ ወሳኝ ነው አሉ ምሁራን፡፡
ምሁራኑ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት፥ ከፋፋይ ትርክትን በመተው የወል ጉዳይ ላይ ማተኮር የሀገርን ሰላም ለማፅናት ከፍተኛ አበርክቶ ያበረክታል፡፡
የወል ትርክት ሰላምና አንድነትን የሚያፀና መሆኑን የሚገልጹት በመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ መምህርና ተመራማሪ ፀጋዬ ሞሮዳ፥ ነጣጣይ ትርክቶችን በመተው አንድነትን በሚያፀና የጋራ ጉዳይ ላይ ማተኮር ይገባል ብለዋል።
ህዝቡ የጋራ ጥቅሙን ለማስጠበቅ ወደ ኋላ እንደማይል ገልጸው፥ ለዚህ ሀገራዊ ዓላማ ሁሉም ሊተባበር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊና ስነሰብ ኮሌጅ ምክትል ዲን ሰለሞን በርሄ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያውያን ኅብረ-ብሄራዊ አንድነትን የሚያጠናክር የወል ትርክትን መሰረት አድርገው መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ከታሪክ፣ ከህልሞቻቸው ብሎም ከሀገራዊ ጥቅሞች የሚመዘዝ የጋራ ማንነት እንዳለቸው ተናግረዋል፡፡
የጋራ እሴታችን ምድረ ቀደምት እንድንባልና ጠንካራ ሀገረ መንግስት እንድንመሰረት ጉልበት ሆኖናል የሚሉት ምሁራኑ፥ ብዝሃነትን ያከበረ የወል ትርክት ላይ ማተኮር ይገባል ነው ያሉት።
በነፃነት ሰለሞን

