Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የዲዚ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ “ከይ ቢያርግ”

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዲዚ ብሔረሰብ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምዕራብ ኦሞ ዞን በማጅ እና በቤሮ ወረዳዎች ይገኛል።

‘ከይ ቢያርግ’ የብሔረሰቡ የዘመን ወለወጫና የምስጋና በዓላቸው ሲሆን÷ በብሔረሰቡ ቋንቋ የብርሃን ዓመት ማለት ነው።

በዓሉ በጥር ወር የመጨረሻ ቀናት ይከበራል። ወቅቱም የክረምቱ ጭጋግ አልፎ ብሩህ ፀሐይ የሚወጣበት፣ ጎተራዎች በበረከት የሚሞሉበት እና የሰው ልጅ ከፈጣሪው ጋር በምስጋና የሚገናኝበት የሽግግር ወቅት ነው።

የዲዚ ብሔረሰብ ለዘመናት ጠብቆ ያቆያቸው የጥበብ፣ የሥርዓት እና የፍቅር እሴቶች በታላቁ “ከይ ቢያርግ” በዓል ዳግም ይደምቃል።

የዲዚና የአካባቢው ምሁራን የጥናትና ምርምር ማህበር ሰብሳቢ አቶ መቱ አኩ በአዲሱ ዓመት የብስራት ዘመን በዲዚዎች ቅሬታዎች የማይሰሙበት፣ ሠላምና ፍቅር የሚፀናበት፣ ልጃገረዶች የሚታጩበት፣ ችግርና ረሃብ የሚወገድበት የመስጠት ወቅት መሆኑን አስረድተዋል።

ከበሮና ክራር ለዘፈን የሚወጣው በአዲሱ ዓመት መሆኑን ገልጸው÷ ይህም በዘፈንና በጨዋታ የምርት ወቅት እንዳያልፍ በማሰብ እንደሆነ ተናግረዋል።

በአዲሱ ዓመት የክራር ቅኝቱ ይከራል፤ ከበሮው ይደምቃል ሲሉም አመልክተዋል።

የከይ ቢያርግ በዓል አከባበር ከተቋረጠ ረጅም ዓመት በኋላ ዳግም በተደራጀ መልኩ የዲዚን ሕዝብ ባህላዊ እሴቶችን ባጎላ መልኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በጥር ወር መጨረሻ በቤሮ እና በማጅ ወረዳዎች ይከበራል።

በዓሉ የዲዚ ብሔረሰብን እንግዳ ተቀባይነትና ወንድማማችነትን በሚያጎላ መልኩ የብሔረሰቡ አባላት፣ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በአደባባይ እንደሚከበርም ተገልጿል።

በተራመድ ጥላሁን

Exit mobile version