አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገር አቀፍ የአዳጊ ወጣቶች ስፖርት ስልጠና እና ምዘና ውድድር በኦሮሚያ ክልል አስተናጋጅነት በአዳማ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
“የአዳጊ ስፖርተኞች ልማት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው ውድድር መክፈቻ ሥነ ሥርዓት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ይገኛል።
በመክፈቻ መርሐ ግብሩ ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስር ሸዊት ሻንካ እንዳሉት÷ የሀገርን ገጽታ ለመገንባት እና አንድነትን ለማጠናከር ስፖርት የላቀ ፋይዳ አለው፡፡
መንግሥት ለአዳጊዎች ስፖርት ልዩ ትኩረት መስጠቱን ገልጸው፤ ይህም በቀጣይ ለታቀደው ተወዳዳሪ ብሔራዊ ቡድን ግንባታ ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል።
የአዳጊ ወጣቶች ስፖርት ስልጠና እና ምዘና ውድድር ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ቁልፍ ሚና አለው ያሉት ሚኒስትሯ÷ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚደረገው በዚህ ውድድር ሁሉም ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ተሳትፎ እንዳላቸው ጠቁመዋል።
በውድድሩ ከ3 ሺህ በላይ ልዑካን በ15 የስፖርት አይነቶች ከዛሬ ጀምሮ ለስምንት ተከታታይ ቀናት ያወዳደራሉ።
በሙባረክ ፋንታው

