Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቅድመና ድህረ ወሊድ አገልግሎት መጠናከር በጤና ተቋም የሚወልዱ እናቶችን ቁጥር አሳድጓል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቅድመ ወሊድና ድህረ ወሊድ አገልግሎት መጠናከር በጤና ተቋም የሚወልዱ እናቶችን ቁጥር አሳድጓል አለ የክልሉ ጤና ቢሮ።

“ፈጠራና ዘላቂ ፋይናንስ ለጤናማ እናትነት” በሚል መሪ ሀሳብ የጤናማ እናትነት ወር በክልሉ ቡታጅራ ጠቅላላ ሆስፒታል ተከብሯል።

የቢሮው ኃላፊ ሳሙኤል ዳርጌ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በክልሉ ለእናቶች ጤና ልዩ ትኩረት በመስጠት አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

በዚህም አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልጸው፥ የቅድመ ወሊድና ድህረ ወሊድ አገልግሎት መጠናከር በጤና ተቋም የሚወልዱ እናቶች ቁጥር እንዲጨምር አስችሏል ብለዋል።

እናቶችን በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም የሚያደርሱ ከ2 መቶ በላይ አምቡላንሶች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።

ህብረተሰቡን በማስተባበር ለእናቶች ጤና አገልግሎት የሚውሉ ሀብቶችን በማሰባሰብ የጤና ተቋማትን በግብዓት የማሟላት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡

በጤና ተቋማት ምቹ የነብሰ ጡር እናቶች ማረፊያ በመገንባት ረገድ የተሻለ አፈፃፀም መመዝገቡን ገልጸው፥ በቀጣይ የላቀ ውጤት ለማምጣት ከሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት የሚከናወኑ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።

በአቢይ ጌታሁን

Exit mobile version