Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በእግር ኳስ ሕይወቱ 13ኛ ክለቡን የተቀላቀለው ሮድሪጌዝ…

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከ2014 የብራዚል ዓለም ዋንጫ በኋላ በምርጥ ብቃቱ መቀጠል ያልቻለ ተጫዋች ነው ኮሎምቢያዊው የፊት መስመር ተጫዋች ሀሜስ ሮድሪጌዝ፡፡

በፈረንጆቹ 1991 የተወለደው ሀሜስ ሮድሪጌዝ እግር ኳስን መጫወት የጀመረው በሀገሩ ክለብ ኢንቪጋዶ ነው፡፡

ከዚያ በመቀጠል በተለያዩ ሊጎችና ክለቦች መጫወት የቻለ ሲሆን የተጠበቀውን ያህል ውጤታማ መሆን አልቻለም፡፡

ሀሜስ ለሪያል ማድሪድ፣ ባየርን ሙኒክ፣ ፖርቶ፣ ሞናኮ፣ ኤቨርተን እና ኦሎምፒያኮስን ለመሳሳሉ ክለቦች ተጫውቶ አሳልፏል፡፡

ተጫዋቹ እነዚህን ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ ለተለያዩ ክለቦች ተጫውቶ ቢያሳልፍም በእግር ኳስ ሕይወቱ ምርጡን ጊዜ ያሳለፈው ከሀገሩ ኮሎምቢያ ጋር በ2014ቱ የዓለም ዋንጫ ነው፡፡

በፈረንጆቹ 2014 በብራዚል አስተናጋጅነት በተካሄደው የዓለም ዋንጫ ክስተት ከነበሩ ተጫዋቾች መካከል ኮሎምቢያዊው ሀሜስ ሮድሪጌዝ ትልቁ ክስተት ነበር፡፡

በወቅቱ ጀርመን ዋንጫውን ስታሸንፍ ሀሜስ ሮድሪጌዝ ደግሞ የስፖርት ቤተሰቡን ልብ ማሸነፉ ይታወሳል፡፡

በወቅቱ 22 ዓመቱ ላይ ይገኝ የነበረው ተጫዋቹ ብራዚላውያን በደገሱት የዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ በውብ ግቦች ደጋፊውን እያዝናና የእርሱን ያህል የነገሰ አልነበረም።

በውድድሩ ከሀገሩ ጋር እስከ ሩብ ፍጻሜ መጓዝ የቻለ ሲሆን፥ ስድስት ግቦችን በማስቆጠር የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን የወርቅ ጫማ አሸናፊም ነበር፡፡

ኮሎምቢያዊው ኮከብ በወቅቱ ካስቆጠራቸው ሰድስት ግቦች መካከል ዩራጋይ ብሔራዊ ቡድን ላይ ያስቆጠራት ግብ የዓለም ዋንጫ በመጣ ቁጥር በእግር ኳሱ ቤተሰብ የምትታወስ ከምርጦቹ አንዷ ሆና ተመዘግባለች፡፡

ይህቺ ግብ ምርጥ ግብ በመባል የፑሽካሽ ሽልማት አሸናፊ እንደነበረች ይታወሳል፡፡

በውድድሩ ላይ ባሳየው ምርጥ ብቃት ተጫዋቹ ከዓለም ዋንጫው ሳይመለስ ታላላቅ ክለቦች የግላቸው ሊያደርጉት ብርቱ ፉክክር ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡

በዓለም ዋንጫው የተለያዩ ሀገራት ደጋፊዎች ልብ ውስጥ የቀረውን ጥበበኛ የስፔኑ ክለብ ሪያል ማድሪድ የግሉ አደረገው፡፡

ሆኖም ብዙ የተወራለትና ሪያል ማድሪድ ከበርካታ ክለቦች ነጥቆ የግሉ ያደረገው ተጫዋች በተጠበቀው ልክ ስኬታማ መሆን አልቻለም፡፡

ከ2014/15 እስከ 2019/20 የማድሪድ ንብረት ሆኖ በቆየባቸው ጊዜያት ለሁለት የውድድር ዓመት ያህል በውሰት ወደ ሙኒክ አቅንቶ ተጫውቷል፡፡

በሪያል ማድሪድ ቆይታው የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግን ጨምሮ በዋንጫ የታጀቡ ዓመታትን ማሳለፍ ቢችልም የእሱ ሚና ግን በተጠበቀው ልክ አልነበረም፡፡

ትልቅ ደረጃ ይደርሳል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ሀሜስ ሮድሪጌዝ እንደተጠበቀው ሳይሆን ከክለብ ክለብ እየዞረ 34 ዓመቱ ላይ ደርሷል፡፡

የ2014ቱ የብራዚሉ ዓለም ዋንጫ ክስተት የነበረው ሮድሪጌዝ አሁን መዳረሻው የአሜሪካ ሜጀር ሊግ ሶከሩ ክለብ ሚኔሶታ ዩናይትድ ሆኗል፡፡

ሀሜስ እስከ 2026 ሐምሌ ወር ድረስ በሚኔሶታ ዩናይትድ የሚያቆየውን ውል የፈረመ ሲሆን፥ በእግርኳስ ሕይወቱ 13ኛ ክለቡ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

Exit mobile version