አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት 4 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ገቢ አገኘሁ አለ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መሥፍን ጣሰው የስድስት ወራት አፈጻጸም አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ አየር መንገዱ ዕድገት ተኮር ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል ብለዋል፡፡
በግማሽ ዓመቱ ሶስት ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን ለመጨመር አቅዶ መስራቱን ጠቅሰው፤ በዚህም ወደ ፖርቶ፣ ሀኖይ እና አቡዳቢ በረራዎችን በይፋ በመጀመር ዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹን 145 ማድረሱን አብራርተዋል፡፡
በሀገር ውስጥም በበጀት ዓመቱ የተመረቀውን የያቤሎ አውሮፕላን ማረፊያ ጨምሮ በ23 ከተሞች የበረራ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
አየር መንገዱ በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት 7 አዳዲስ አውሮፕላኖችን ያስገባ ሲሆን ተጨማሪ አዳዲስ አውሮፕላኖችን ለማስገባት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
በመጀመሪያው ስድስት ወራት 10 ነጥብ 64 ሚሊየን መንገደኞችን በማጓጓዝ ዕቅዱን ሙሉ በሙሉ ማሳካቱን ጠቅሰው፤ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ11 በመቶ ጭማሪ ማስመዝገቡን አስረድተዋል፡፡
በጭነት አገልግሎት ዘርፍ 451 ሺህ ቶን ጭነት በማጓጓዝ ከዕቅዱ 4 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን አመልክተዋል፡፡
የአየር መንገዱ አጠቃላይ አፈጻጸም ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ብልጫ ማስመዝገቡን ገልጸው፤ በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት 4 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አብራርተዋል፡፡
የተለያዩ አዳዲስና የማስፋፊያ ፕሮጀክቶችን እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ቅርቡ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠለት የቢሾፍቱ አየር ማረፊያ ምዕራፍ አንድ ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው ብለዋል።
አየር መንገዱ የሚያስገነባው አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት አጠቃላይ ግንባታ 42 በመቶ ደርሷል ነው ያሉት፡፡
አራት አዳዲስ ተጨማሪ መዳረሻዎችን እየገነባ መሆኑን የገለፁት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ከአራቱ ሶስቱን አዲስ መዳረሻዎች በሚያዚያ ወር ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በመሳፍንት ብርሌ

