አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከኡጋንዳ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ ኦርየም ሄንሪ ኦኬሎ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው በ48ኛው የአፍሪካ ኅብረት የሥራ አስፈጻሚዎች ስብሰባና በ39ኛው የመሪዎች ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ በዛሬው ዕለት አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች ባደረጉት ውይይት ሀገራቱ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው በመግለጽ ይህንን ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡
ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ሁለቱ ሀገራት ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰው፥ በቀጣይም የሀገራቱን ህዝቦች ተጠቃሚ በሚያደርጉ ሁለንተናዊ ዘርፎች ትብብራቸውን ማጠናከር የሚቻልበትን አግባብ አብራርተዋል።
የኡጋንዳ ውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ ኦርየም ሄንሪ ኦኬሎ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ በመሪዎቻቸው መካከል ጠንካራ ግንኙነት መመስረታቸውንና በቀጣናው ጉልህ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት አጠናክራ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኗንም አረጋግጠዋል።

