Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የማቴይ እቅድ በኢትዮጵያና ጣልያን መካከል ያለውን ትብብር ያጠናክራል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የማቴይ እቅድ በኢትዮጵያ እና ጣልያን መካከል ያለውን ስልታዊ ትብብር ያጠናክረዋል አሉ በውጭ ጉዳይ ኢንስትቲዩት የአሜሪካና አውሮፓ ጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት የደቡብና ምስራቅ አውሮፓ ቀጣና ተመራማሪ ታሪኩ አብርሃ።

የጣሊያን አፍሪካ ጉባዔ በመጪው የካቲት 6 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

ተመራማሪው ከፋና ፖድካስት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት÷ የጣሊያን አፍሪካ ጉባዔ በአዲስ አበባ መካሄድ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስኬት ነው።

በፈረንጆቹ 2024 በሮም በተካሄደው የጣልያን አፍሪካ ጉባዔ ላይ ይፋ ከተደረጉ ቁልፍ ማዕቀፎች አንዱ የማቴይ እቅድ ጣልያን ከአፍሪካ ጋር ያላት የኢኮኖሚ እና የልማት ትብብር ለማጠናክር ያለመ መሆኑን አንስተዋል።

የማቴይ እቅድ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን መከላከል፣ ጤና፣ ሃይል አቅርቦት እና መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ በትኩረት የሚሰራ ፕሮጀክት ነው።

ጣልያን ከዚህ ቀደም ከአፍሪካ ጋር የነበራት ግንኙነት በተለይ በእርዳታ ላይ ያተኮረ እንደነበር ጠቁመው÷ አሁን ግን የጋራ እድገት እና የጋራ ፍላጎት ላይ የተመረኮዘ ግንኙነት አዲሱ የትብብር ምዕራፍ ሆኗል ብለዋል።

ጣልያን በማቴይ እቅድ ስልታዊ አጋር ካደረገቻቸው ስምንት የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ አንዷ ኢትዮጵያ ናት፤በማቴይ እቅድ ውስጥ ኢትዮጵያ ተመራጭ እና ተጠቃሚ መሆኗ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ስልታዊ ትብብር እንደሚያጠናክረው ተናግረዋል።

ይህም የኢኮኖሚ እና የልማት ትብብር ላይ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ነው ተመራማሪው ያስገነዘቡት፡፡

ሰጪ እና ተቀባይ አይነት ሳይሆን የጋራ እድገት እና የጋራ ፍላጎት ላይ የተመረኮዘ ሚዛናዊ ግንኙነት አዲሱ የጣልያን እና የአፍሪካ የትብብር ምዕራፍ እንደሆነ አስረድተዋል።

በብርሃኑ አበራ

ተመራማሪው ታሪኩ አብርሃ ከፋና ፖድካስት ጋር ያደረጉትን ቆይታ ለመከታተል ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ👇 https://www.youtube.com/watch?v=CnX3Yn_ECek

Exit mobile version