አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት የመንግሥትና የፓርቲ ስራዎች ድጋፋዊ ሱፐርቪዥን ማጠቃለያ መድረክ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህን ጨምሮ የፓርቲና የመንግሥት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
አቶ አደም ፋራህ ስለድጋፋዊ ሱፐርቪዥን ዓላማ በማብራራት በመድረኩ በብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ2018 ዓመታዊ የከፍተኛ አመራር ስልጠና ማጠቃለያ የተቀመጡ አቅጣጫዎችና የስራ መመሪያዎች አፈጻጸም እንደሚገመገም ተናግረዋል።
በመድረኩ የድጋፋዊ ሱፐርቪዥን አባላት በምልከታቸው ያገኟቸውን ተሞክሮዎች የጋራ ማድረግና በቀጣይነት በፌዴራል መንግሥት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች እንደሚለዩ አመልክተዋል።
በተጨማሪም የድጋፋዊ ሱፐርቪዥን አባላት በሁሉም ክልሎችና ሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች ባለፉት ስድስት ወራት በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት መከናወናቸው ተመላክቷል።
በዚህም አባላቱ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ፣ ከተረጂነት ለመውጣት፣ ከኮሪደር ልማት፣ ኢንዱስትሪ እና የልማትና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ የተከናወኑ ስራዎችን አፈጻጸም አቅርበው ግምገማ ይደረግባቸዋል ነው የተባለው።

