Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሐረሪ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሐረሪ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት 9ኛ መደበኛ ጉባኤውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በተገኙበት እያካሄደ ይገኛል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት የግማሽ በጀት አመት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ እንዳሉት፥ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥና ዘላቂ ሰላምን በማፅናት የክልሉን ነዋሪዎች ተጠቃሚነት ያረጋገጡ የልማት ስራዎች ተከናውነዋል።

የህዝቡን መሠረታዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው፥ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው በጀትና ጊዜ ጥራታቸውን ጠብቀው እንዲጠናቀቁ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

የሐረር ከተማ የኮሪደር ልማትና የተለያዩ መሠረተ ልማቶች ዝርጋታ የከተማዋ የቱሪስት ፍሰት እንዲጨምር አስችሏል ያሉ ሲሆን፥ በግማሽ በጀት አመቱ 7 ሺህ የሚጠጉ የውጭና ከ95 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ክልሉን መጎብኘታቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ በግማሽ በጀት ዓመቱ ከ54 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ መሰረተ ልማት ማከናወን መቻሉንም አንስተዋል፡፡

ሐረር መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎትን ወደ ተግባር በማሸጋገር ከነዋሪው በተደጋጋሚ ለሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ተጨባጭ ምላሽ መስጠት መጀመሩንም ነው የገለጹት፡፡

ምክር ቤቱ በርዕሰ መስተዳድሩ በቀረበው ሪፖርት ላይ እየተወያየ ሲሆን፥ በጉባኤው ላይ የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችን ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በተስፋዬ ኃይሉ

Exit mobile version