Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ ዲጂታላይዜሽን ትራንስፎርሜሽን ለአባል ሀገራት በተሞክሮነት የሚቀርብ ነው – የአፍሪካ ሕብረት

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የዲጂታላይዜሽን ትራንስፎርሜሽን ለአባል ሀገራት በተሞክሮነት የሚቀርብ ነው አለ የአፍሪካ ሕብረት።

የሕብረቱ የግብርና፣ ገጠር እና ዘላቂ ልማት ኮሚሽነር ሞሲስ ቪላካቲ ከሕብረቱ የስራ አስፈፃሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ ጎን ለጎን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም የሕብረቱ ስብሰባ መሪ ሐሳብ ከሆነው “የውሃ ደኅንነት እና የንጽህና አጠባበቅ፤ የአጀንዳ 2063” ትግበራ ዙሪያ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን አብራርተዋል።

በማብራሪያቸው የአጀንዳ 2063 አተገባበር፣ የካምፓላ ስምምነት እንዲሁም የግብርና ዲጂታላይዜሽን ስራዎችን ተመልክተዋል።

የግብርና ዲጂታላይዜሽን የአፍሪካ የለውጥ አቅም በመሆኑ ሕብረቱ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዲጂታላይዜሽን የግብርናው ዘርፍ አጋዥ እየሆነ መጥቷል ያሉት ኮሚሽነሩ÷ ይህም ተሞክሮ ለሌሎች ሀገራት ልምድ እንደሚሆንና በአባል ሀገራት መካከል በጋራ መስራት የሚቻልባቸውን ዕድሎች መፍጠር እንደሚገባ አመልክተዋል።

አፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅባት በመጠቆም የኢትዮጵያ ስንዴን በራስ አቅም የማምረት ብሎም ወደ ወጪ ንግድ የመቀየር ብቃት የሚደነቅ መሆኑን አብራርተዋል።

በቀጣይነትም አፍሪካ በዋና ዋና ሰብሎች ላይ ምርታማነትን ልትጨምር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በሰለሞን በየነ

Exit mobile version