Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሕገ ወጥ መንገድ ገንዘብ በማስተላለፍ ኢትዮጵያ ከ7 ሚሊየን ዶላር በላይ እንድታጣ በማድረግ የተጠረጠረ ቻይናዊ ተከሰሰ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ውጭ የባንክ ስራ በመስራት ኢትዮጵያ ከ7 ሚሊየን ዶላር በላይ እንድታጣ በማድረግ የተጠረጠረ ቻይናዊ ክስ ተመሰረተበት።

የክስ መዝገቡን የተመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ልዩ ልዩ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

ተከሳሹ ቸን ዥኳንግ የባንክ ስራ አዋጅ ቁጥር 1360/2017 አንቀጽ 2 (6) መ 3 (1) እና 90 (1) ስር የተመላከተውን በመተላለፍ የወንጀል ድርጊት መፈጸሙን በመግለጽ ነው ዐቃቤ ሕግ ክስ ያቀረበው።

በዚህም ተከሳሹ የባንክ ስራ ለመስራት ከብሔራዊ ባንክ የተሰጠ ህጋዊ ፍቃድ ሳይኖረዉ በውጭ ሀገራት የሚገኙ ግለሰቦች ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ መላክ ሲፈልጉ ካልተያዙ ግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን ገንዘቡን በመሰብሰብ የሚላክላቸዉን ሰዎች ስም ዝርዝር የባንክ ሂሳብ ቁጥር እና የገንዘቡን መጠን በሚያስተላልፉበት መረጃ መሰረት ገንዘቡን ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ 18 ግለሰቦች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በአቢሲኒያ ባንክ እና በአዋሽ ባንኮች በኩል ገንዘብ ማስተላለፉን ዐቃቤ ሕግ በክስ ዝርዝሩ አመልክቷል።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በስሙ የከፈታቸዉን የሂሳብ ቁጥሮች በመጠቀም ከሐምሌ 25 ቀን 2010 ዓ.ም እስከ ሕዳር 4 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ለ2 ሺህ 271 ጊዜ 570 ሚሊየን ዶላር ከውጭ ሀገራት ገንዘብ ለተላከላቸው ሰዎች ማስተላለፉን ገልጿል።

ይህ ገንዘብ በህጋዊ መንገድ ወደ ሀገር ቢገባ ኢትዮጵያ በወቅቱ በነበረው ምንዛሪ መሰረት ታገኝ የነበረውን 6 ሚሊየን 600 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ማሳጣቱን ጠቅሷል።

ተከሳሹ በአቢሲኒያ ባንክ በስሙ የከፈታቸውን የሂሳብ ቁጥሮች በመጠቀም ከሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም እስከ ሕዳር 4 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ 60 ጊዜ 32 ሚሊየን 600 ሺህ ዶላር ለተላካላቸዉ ሰዎች ገንዘብ ማስተላለፉን ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው የክስ ዝርዝር አንስቷል።

ይህ ገንዘብ በህጋዊ መንገድ ቢተላለፍ ኖሮ ኢትዮጵያ 454 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ታገኝ እንደነበረ ያነሳው ዐቃቤ ሕግ፤ በአጠቃላይ ተከሳሹ በስሙ በከፈታቸዉ የባንክ ሂሳብ ቁጥሮች 603 ሚሊየን 424 ሺህ ብር ከዉጭ ሀገራት ዶላር ለተላከላቸዉ ሰዎች አስተላልፏል ብሏል።

ይህም በአጠቃላይ በወቅቱ በነበረዉ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሲሰላ 7 ሚሊዮን 153 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የውጭ ምንዛሪ ኢትዮጵያ እንድታጣ በማድረግ ያለ ብሔራዊ ባንክ ፍቃድ የባንክ ስራ መስራት ወንጀል ተከሷል፡፡

በመቅደስ ከበደ

Exit mobile version