አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፓርቲዎች የዴሞክራሲ መርህን ተከትለው በውይይት ላይ የተመሰረተ የሰለጠነ ፖለቲካ ማራመድ እንደሚገባቸው ተመላከተ።
በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች “ለሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በጋራ እንቁም” በሚል መሪ ሐሳብ በባሕር ዳር ከተማ ምክክር እያካሄዱ ነው።
የአማራ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ተስፋሁን ዓለምነህ ሁሉም ፓርቲዎች ሐሳባቸውን እኩል እንዲያቀርቡ እድሉ እየተመቻቸ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከምቹ መደላድሎች መካከል ደግሞ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የምክክር መርሐ ግብሮች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
ፓርቲዎች በምክር ቤታቸው ጉዳዮችን በግልጽነት በመወያየት ምርጫው ነጻ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አስገንዝበዋል።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ተሳታፊ የሚሆኑት ፓርቲዎች በምርጫው የቅስቀሳና የትውውቅ ሂደት የሚፈጠሩ ጉዳዮችን በውይይትና ምክክር ለመፍታት ከወዲሁ ዝግጅት እንዲያደርጉም ተናግረዋል።
ፓርቲዎች ከምርጫ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ድህረ ምርጫ የሚያጋጥሙ ጉዳዮችን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የመፍታት ኃላፊነት አለባቸው ያሉት ደግሞ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ መስፍን አበጀ (ዶ/ር) ናቸው።
በምርጫ ጊዜ የህግ የበላይነትን አክብሮ መሥራትና ዳኝነቱን ለሕዝብ መስጠት እንደሚገባ ገልጸው÷ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም ፓርቲዎች በቂ ዝግጅት ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።
በደሳለኝ ቢራራ

