አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት 2 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ኢንቨስትመንት ወደ ሀገር ውስጥ መሳብ ተችሏል አለ።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) እንዳሉት÷ በኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚታዩ ማነቆዎችን ለመፍታት እንደ ሀገር በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።
የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለማሳደግ ከሦስተኛ ወገን የፀዳ መሬት በማዘጋጀትና የአሰራር ክፍተትን በመሙላት በባለሃብቱ ዘንድ የነበረው ቅሬታ መፈታቱን ጠቅሰው÷ በዚህም የውጭ ምንዛሪ አድጓል ብለዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት በተሰራው ሥራም 2 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ወደ ሀገር ውስጥ መሳብ እንደተቻለና ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ20 በመቶ በላይ ጭማሪ ማሳየቱን አመልክተዋል።
በዘርፉ በርካታ ስራዎች ቢሰሩም ኢትዮጵያ ካላት እምቅ ሀብት አንፃር የበለጠ ለማሳደግ መረባረብ ያስፈልጋል ብለዋል።
በስድስት ወራት ለ245 የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱም ተመላክቷል።
በሰብለ አክሊሉ

