Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከ163 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ተፈጥሯል – አቶ ጥላሁን ከበደ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በክልሉ በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ከ163 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ተፈጥሯል አሉ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ጉባዔ በአርባ ምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው።

አቶ ጥላሁን ከበደ የክልሉን የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት እያቀረቡ ነው።

በሪፖርታቸው እንዳመለከቱት፤ በተለያዩ ዘርፎች ስኬታማ ተግባራት ተከናውነዋል።

በ2017/18 ምርት ዘመን የበልግ የእርሻ 868 ሺህ 730 ሄክታር መሬት በማልማት ከ81 ሚሊየን በላይ ኩንታል ምርት ተሰብስቧል ብለዋል።

እንዲሁም በ2018 ዓ.ም በበጋ መስኖ ልማት በሁለት ዙር 155 ሺህ 812 ሄክታር መሬት በማልማት 38 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱንም አስረድተዋል።

ከ19 ሺህ ቶን በላይ የታጠበ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ መቻሉንም ተናግረዋል።

በእንስሳት ሀብት ልማት ዝርያ በማሻሻል ተግባር 113 ሺህ 130 ከብቶች ተዳቅለዋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ 286 ነጥብ 7 ሚሊየን ሊትር ወተት ተመርቷል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ለፋና ዲጂታል ገልጿል።

በተፈጥሮ ሀብት ልማት ዘርፍ በተለያዩ የክረምት መርሐ ግብሮች 226 ሚሊየን 301 ሺህ 580 ችግኞች መተከላቸውን ገልጸው፤ ከ90 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በደንና በጥምር ደን ተሸፍኗል ነው ያሉት።

በከተማ እና በገጠር 354 ሺህ 606 ስራ አጥ ዜጎችን መለየታቸውን ጠቅሰው፤ በተለያዩ የስራ ዘርፎች ለ163 ሺህ 586 ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል።

ለ7 ሺህ 17 ዜጎች የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት መፈጠሩን ገልጸው፤ በተለያዩ የስራ ዘርፎች ለመሰማራት የተደራጁ ኢንተርፕራይዝ አባላት 141 ሚሊየን 856 ሺህ 263 ብር እንዲቆጥቡ ተደርጓል ነው ያሉት።

Exit mobile version