አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ የአፍሪካ መሪዎች የውህደትና የትብብር መርሐ ግብሮችን ማጠናከር አለባቸው አሉ።
39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ “ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ፥ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀ መንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ የአፍሪካ የፋይናንስ ተቋማት የአህጉሪቱን ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ለማፋጠንና የረዥም ጊዜ የልማት ግቦቿን ለማሳካት ትብብራቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል ብለዋል፡፡
ተቋማቱ ስትራቴጂያዊ አህጉራዊ ፕሮግራሞችን ለመደገፍ ተቀራርበው መስራት አለባቸው ያሉት ሊቀመንበሩ፥ አፍሪካ ከዓለም ኢኮኖሚዎች ጋር ለመወዳደር አቅሟን ማጠናከር እንደሚጠበቅባት አስገንዝበዋል፡፡
አጀንዳ 2063 ጠንካራና የበለጸገች አፍሪካን ለመገንባት መሪ ማዕቀፍ ሆኖ እንደሚቀጥል ጠቁመው፥ ወጣቶችንና ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፈጣን የኢንዱስትሪ ልማት፣ የግብርና ትራንስፎርሜሽን፣ የኢነርጂ ልማትና መሠረተ ልማትን ማስፋፋት ይገባል ነው ያሉት፡፡
ግጭቶችና ህገመንግስታዊ ያልሆኑ የመንግስት ለውጥ ሙከራዎች የአህጉሪቱን ሰላምና መረጋጋት እየፈተኑ እንደሆነ አንስተው፥ ይህን ለመቅረፍ የአህጉሪቱ መሪዎች ውህደትና ትብብርን በማጠናከር ለሰላምና ልማት ቁርጠኝነት እንዲያሳዩም ጠይቀዋል።
በሶስና አለማየሁ

