Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

‎ለአፍሪካውያን የሚተርፍ ልማት፣ ዕድልና ክብርን የሚያረጋግጥ የአፍሪካ ሕብረት እንዲኖር…

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአፍሪካ እና የዓለም አቀፍ መሪዎችን ወደ ኢትዮጵያ እንኳን በደኅና መጣችሁ በማለት፣ የአፍሪካን ታሪካዊ ዐሻራ እና ጽኑ ርዕይ አፅንዖት ሰጥተው ገልጸዋል።

‎የአኅጉሩ ትልቁ ሀብት የተፈጥሮ ጸጋ ብቻ ሳይሆን፣ ጠንካራ ተቋማትን የመገንባት፣ ፈጠራን የማሳደግ እና ለዘላቂ ልማት ያለው አስተዳደራዊ ችሎታ መሆኑን አሳስበዋል።

በውኃ ልማት፣ በኢነርጂ፣ በምግብ ዋስትና እና በኢንዱስትሪ ልማት ረገድ እየታዩ ያሉ መሻሻሎችን በማንሳት፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ በስንዴ ምርት ራስን የመቻል ጥረትን እና እየተስፋፉ ያሉ የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንቶችን ለአፍሪካዊ መፍትሔዎች እና ለጋራ ብልጽግና ማሳያ ተጨባጭ ምሳሌዎች አድርገው ጠቅሰዋል።

‎አኅጉሩ የደረሰበት ጠንካራ የዕድገት ጉዞ፣ የኢትዮጵያን የ10 ነጥብ 2 በመቶ ተጠባቂ ዕድገት እንዲሁም የአኅጉሩን የሥነ ሕዝብ ብልጫ ለመጠቀም በወጣቶች፣ በጤና እና በትምህርት ላይ ኢንቨስት ማድረግ ያለውን አስፈላጊነት ገልጸዋል።

‎በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አማካኝነት የሚታየውን የአየር ንብረት መሪነት፣ በ”ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030″ ሥር እየተከናወነ ያለውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የታዩ ስኬቶችን እና የአኅጉራዊ ትስስር መስፋፋትን አጉልተዋል።

በመጨረሻም ዓለም አቀፋዊ አጀንዳዎችን የመቅረጽ አቅም ያለው እና ለሁሉም አፍሪካውያን የሚተርፍ፤ ልማትን፣ ዕድልን እና ክብርን የሚያረጋግጥ በራሱ የሚተማመንና የተባበረ የአፍሪካ ሕብረት እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል፡፡

#AUSummit
#PMOEthiopia

Exit mobile version