Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል በተከናወኑ ሥራዎች የተገልጋይን እርካታ ማሳደግ ተችሏል – አቶ አወሉ አብዲ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል በተሰሩ ሥራዎች የተገልጋይን እርካታ መጨመር ተችሏል አሉ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አወሉ አብዲ ።

በጨፌ ኦሮሚያ 6ኛ የሥራ ዘመን 5ኛ ዓመት 10ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አቶ አወሉ አብዲ ለጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት እንደገለጹት÷ የክልሉ መንግሥት በየደረጃው አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል በሰራው ሥራ ተጨባጭ ውጤት እየመጣ ነው።

በተለይም አገልግሎቶችን ወደ ተጋልጋዩ ማሕበረሰብ ለማቅረብ ይቻል ዘንድ አዲስ የቀበሌ አደረጃጀት ተዘርግቶ ውጤታማ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም ከ7 ሺህ በላይ ቀበሌዎችን በማዋቀር 54 ሺህ አመራር እና ባለሙያ መመደቡን ጠቅሰው ÷ ምቹ የሥራ ቦታ ለመፍጠር ጥረት ተደርጓልም ነው ያሉት።

በከተሞችም መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተግባራዊ በማድረግ በርካታ አገልግሎቶች በአንድ ቦታ በቴክኖሎጂ ታግዘው እየተሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።

ቀድመው አገልግሎት መስጠት በጀመሩ አምስት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማዕከላት ውስጥ ከ400 ሺህ በላይ የክልሉ ነዋሪዎች አገልግሎት ማግኘታቸውን አስረድተዋል።

እስካሁን በክልሉ በከተሞችም ሆነ በገጠር በተሰሩ ሥራዎች የተገልጋዩ እርካታ እየጨመረ መምጣቱን ማወቅ መቻሉን ነው ያመለከቱት፡፡

በጨፌው የክልሉ መንግሥት ተጠሪ የሆኑት አቶ ከፍያለው ተፈራ በበኩላቸው÷ በክልሉ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን የተሰሩ ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ አምጥተዋል ብለዋል።

በተለይም የቀድሞ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ የክልሉ ሕዝብ ከመንግስት ጋር በቅርበት በመስራቱ በርካታ ታጣቂዎች ወደ ሰላም መመለሳቸውን አስታውሰዋል።

በጥፋት መንገድ ላይ የሚገኙ አካላት ወደ ሰላም እንዲመጡ የክልሉ መንግሥት አሁንም በትዕግስት እንደሚጠብቅ ገልጸው÷የመንግሥትን የሰላም አማራጭ ወደጎን በማለት የሕዝብ ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ይጠናከራል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

ሕዝቡ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ የድርሻውን እንዲያጠናክር ጠይቀው÷ ሕገ ወጥ ንግድ እና ኮንትሮባንድን ለመከላከል የተቀናጀ ርምጃ እየተወሰደ መሆኑን እና የጨፌው አባላትም ጥረቱን እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት ገንዘብ ቢሮ ሃላፊ አቶ ቶሎሳ ገደፋ÷ በክልሉ የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እና በጀት እንዲጠናቀቁ ክትትል እና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

በክልሉ የሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችም ፍትሃዊነትን ማዕከል ባደረገ መልኩ የህዝብ ተጠቃሚነትን የሚያሳድጉ እንዲሆኑ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

Exit mobile version