Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለአፍሪካ ብልጽግና በውሃ ዘርፍ ላይ በቆራጥነት ኢንቨስት ማድረግ ይገባል – ኮሚሽነር ሞሰስ ቪላካቲ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለአፍሪካ ብልጽግና እና መረጋጋት በውሃ ዘርፍ ላይ በቆራጥነት ኢንቨስት ማድረግ ይገባል አሉ የአፍሪካ ሕብረት የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚ እና የዘላቂ አካባቢ ኮሚሽነር ሞሰስ ቪላካቲ።

ትናንት የተጀመረው የአፍሪካ ሕብረት መሪዎች ጉባኤ ዛሬም በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ውይይቶችን እያደረገ ሲሆን÷ በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽንና ደቡብ አፍሪካ ትብብር የተዘጋጀው የውሃ ኢንቨስትመንት ውይይት እየተካሄደ ነው።

ኮሚሽነር ሞሰስ ቪላካቲ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ ውሃ እና የንጽህና አጠባበቅ ለአፍሪካ ልማትና ለኢኮኖሚ ሽግግር መሰረታዊ ጉዳዮች ናቸው።

በዘርፉ አፍሪካ የገንዘብ እጥረት እንዳለባት ጠቁመው÷ ይህም የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እንቅፋት መሆኑን አንስተዋል።

በጉባኤው በቢሊየን ዶላር የሚቆጠር የኢንቨስትመንት ቃል ኪዳን የተገኘላቸው ፕሮጀክቶች መቅረባቸውን ጠቅሰዋል።

የናሚቢያ ፕሬዚዳንት ኔቱምቦ ናንዲ ዴትዋህ (ዶ/ር) የአፍሪካ የውሃ አቅርቦትና ዘላቂ ንፅህና አስተዳደርን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ንፅህና ክብርን፣ ጤናንና የተሻለ ህይወትን ያረጋግጣል ያሉት ፕሬዚዳንቷ÷ አህጉሪቱ አሁንም በብዙ ማህበረሰቦች ውስጥ መሰረታዊ የንፅህና አገልግሎት ክፍተት እንዳለ ተናግረዋል።

ይህም ለረጅም ጊዜ ትኩረት ተነፍጎት መቆየቱን ተናግረው÷ አሁን ላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መለየቱን ተከትሎ በንፅህና ፕሮግራሞች እና ፕሮጀክቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከሰሃራ በታች ባለው ቀጣና የሚከሰተው የውሃ ችግር ፈተና ሆኖ የዘለቀ መሆኑን በማንሳት÷ ችግሩን ለመፍታት የከርሰ ምድር ውሃ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ወደ ተግባር መቀየር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህንን የውሃ ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ሳይንሳዊ መንገድን ተከትሎ እንዲከወን የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን የተቋሙ ዳይሬክተር ተወካይ በመድረኩ ላይ አረጋግጠዋል።

በመድረኩ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋሙ የውሃ ፕሮግራሞችን እንዲያዘጋጁ የሚያግዙ መመሪያዎችና የኢንቨስትመንት ሂደቱን ለመከታተል የሚያስችል የውጤት መመዝገቢያ ይፋ ተደርጓል።

በይስማው አደራው

Exit mobile version