Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ጉባኤ የዳኞች ሹመትን በማጽደቅ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጨፌ ኦሮሚያ 6ኛ የስራ ዘመን 5ኛ ዓመት 10ኛ መደበኛ ጉባኤ የዳኞችን ሹመት በማጽደቅ ተጠናቀቀ።

የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ገዛሊ አባሲመል ተሿሚ ዳኞችን ለጨፌው ሲያቀርቡ÷ በክልሉ የዳኝነትና ፍትህ አሰጣጥን ለማቀላጠፍ ዘርፉን በሰው ኃይል ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በዘርፉ የሴት ዳኞችን ተሳትፎ ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው÷ ለጨፌው ከቀረቡት 88 የወረዳ ዳኞች ሹመት ውስጥ 26 የሚሆኑት ሴት ዳኞች መሆናቸውን አስረድተዋል።

በተጨማሪም ጉባኤው የኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሮዛ ቢያን ሹመት አፅድቋል።

በሌላ በኩል ጨፌው በብልሹ አሰራር ወንጀል የተጠረጠሩትን የአቶ ገመቹ ደበላ ገነቲን ያለ መከሰስ መብት አንስቷል።

ትናንት ጀምሮ በተካሄደው የጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ጉባዔ ላይ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።

በሪፖርታቸውም መንግሥት ሰላምና ጸጥታን ለማረጋገጥ ባቀረበው የሰላም ጥሪ መሰረት በጫካ የነበሩ ታጣቂዎች በሰላማዊ መንገድ እንዲገቡ መደረጉን ገልጸዋል።

ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ልዩነቶችን በውይይትና በስምምነት ለመፍታት ዝግጁ ለሆኑ ቀሪ የታጠቁ ኃይሎች የተከፈተው የሰላም በር ክፍት መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል በተሰሩ ስራዎች አበረታች ውጤት መመዝገቡንም ተናግረዋል።

በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በገቢ አሰባሰብ፣ በግብርና፣ በአምራች ዘርፍ እንዲሁም በትምህርት እና ጤና ላይ በተሰሩ ስራዎች አመርቂ ውጤት መገኘቱንም አብራርተዋል።

Exit mobile version