Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሴቶችንና የሕጻናትን የትምህርት ተደራሽነት ከፍ ለማድረግ ሰርተናል – ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሴቶችንና የሕጻናትን የትምህርት ተደራሽነት ከፍ ለማድረግ ሰርተናል አሉ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው።

30ኛው የአፍሪካ ቀዳማዊ እመቤቶች የልማት ተቋም ጉባኤ “የአፍሪካን ሴቶች ፈተናዎችን የመቋቋም ዐቅም መገንባት፡- የአየር ንብረት፣ ግጭቶች እና ዘላቂ ነገ” በሚል መሪ ሀሳብ ተካሂዷል።

ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጉባኤውን አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ በጾታ እኩልነት፣ በጤና እና በትምህርት መርሐ ግብሮች፣ በኢኮኖሚው ዘርፍ እና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የአፍሪካ ሴቶችን ዐቅም የበለጠ ማሳደግ ጠቃሚ ሚና አለው ብለዋል፡፡

በተለይ ደግሞ ሴቶችን ማዕከል ያደረጉ የማኅበራዊ ልማት ተግባራት የሴቶችን ዐቅም የበለጠ እንደሚያጎለብቱ አስገንዝበዋል።

ይህንን ታሳቢ በማድረግ በቀዳማዊት እመቤት ፅ/ቤት በኩል ባለፉት ስድስት ዓመታት 37 ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች በተለያዩ አካባቢዎች መገንባታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም የሴቶችን እና የሕጻናትን የትምህርት ተደራሽነት ከፍ ለማድረግ ሰርተናል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ለሴቶች የሙያና የንግድ ክህሎት ሥልጠና፣ የመሥሪያ ቦታ፣ ግብአትና የመነሻ ካፒታል በማመቻቸት ሴቶች በገቢ ማስገኛ ሥራ ላይ ተሠማርተው የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ሕይወት እንዲቀይሩ አድርገናል ነው ያሉት፡፡

ሴቶችን በየዘርፉ ማሳተፍ ሀገርን በሙሉ እንደ ማሳተፍ ይቆጠራል ያሉት ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ፤ የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ ሊሳካ የቻለው ብዙ ሚሊየን ሴቶች በፈቃደኝነት በመሳተፋቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

የአየር ንብረት መዛባትን ለመቋቋምም ሆነ ሌሎች ችግሮችን ለመቅረፍ ሴቶች ወሳኙን ቦታ የሚያገኙበትን ዐውድ መፍጠር አለብን ሲሉ ገልጸው፤ ለዚህ ደግሞ እኛ ቀዳማዊ እመቤቶች ከፍ ያለ ኃላፊነት አለብን ብለዋል፡፡

Exit mobile version