Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአፍሪካ ሀገራትን የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችል የማገገሚያ ዕቅድ እንዲያወጡ መደገፍ ይገባል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገራትን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን መቋቋም የሚያስችል የማገገሚያ ዕቅድ እንዲያወጡ መደገፍ ይገባል አሉ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ።

የኮሚሽኑ ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ የ39ኛው የመሪዎች ጉባዔ መጠናቀቅን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም በአረንጓዴ ዐሻራ ላስመዘገበችው ስኬት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

39ኛው የህብረቱ መሪዎች ጉባዔ በአየር ንብረት ፋይናንስ፣ ተጽዕኖን በመቋቋምና በሀይል ሽግግር የአፍሪካን ድምጽ የሚያንጸባርቅ አቋም የተያዘበት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያሳዩት ቁርጠኝነት በተግባር የሚታይ እንደሆነ ጠቅሰው፤ የተመዘገበውን ውጤት አዲስ አበባ ከተማ በራሷ ትናገራለች ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ባስተናገደችው ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ለአህጉሪቱ አቋም ማጣቀሻ የሚሆን ሰነድ መጽደቁን አስታውሰዋል።

የአፍሪካ የበካይ ጋዝ ልቀት ምጣኔ ዝቅተኛ ቢሆንም በአየር ንብረት ለውጥ ያላት ተጎጂነት ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገራትን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን መቋቋም የሚያስችል የማገገሚያ ዕቅድ እንዲያወጡ መደገፍ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡

Exit mobile version