Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ግልጽ፣ ሚዛናዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሚዲያዎች ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ግልጽ፣ ሚዛናዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሚዲያዎች የበኩላቸውን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል አለ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ የኮሙኒኬሽንና ሚዲያ ተቋማት የምርጫውን ሂደት ስኬታማ ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በወላይታ ሶዶ ከተማ የጋራ ምክክር እያካሄዱ ይገኛል።

የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ኢትዮጵያ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ላይ ተደማሪ ውጤቶች እንድትጎናጸፍ በሚያስችል አኳኋን እንዲካሄድ እየተሠራ ነው።

ምርጫው ግልጽ፣ ሚዛናዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሚዲያዎች የበኩላቸውን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባልም ነው ያሉት።

የምርጫ ሂደቱ ነጻ፣ ፍትሐዊና ሚዛናዊ ሆኖ ዜጎች በመረጡት መንግሥት መመራት እንዲችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በሁሉም የሚዲያ ተቋማትና አማራጮች ሊሠራ እንደሚገባም አመልክተዋል።

በምርጫው ሂደት ሁሉም ድምጾች እንዲስተናገዱ ሚዛናዊነትን የማስጠበቅ ሥራ የሚዲያ ተቋማት ተልዕኮ በመሆኑ አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉ አስገንዝበዋል።

በምርጫው ዜጎች በንቃት እንዲሳተፉ መገናኛ ብዙኃን ትክክለኛ መረጃ በመስጠት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

በአስጨናቂ ጉዱ

Exit mobile version