Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ጎንደር ከተማ በታሪካዊ ስራዎች…

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጎንደር ከተማ በታሪካዊ ስራዎች ይበልጥ እየተገለጠች ነው አሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሴክተሮችና ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ክትትል ሚኒስትር ዴኤታ አክሊሉ ታደሰ (ዶ/ር)።

ሚኒስትር ዴኤታው ይህንን ያሉት በጎንደር ከተማ የፋሲል አብያተ መንግሥት እንዲሁም በከተማዋ የተከናወኑ የኮሪደር ልማት ስራዎችን በጎበኙበት ወቅት ነው።

ጎንደር የኢትዮጵያ ከተሞች ምሳሌ መሆኗን አንስተው÷ የፌዴራል መንግሥት የአማራ ክልል የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን ለማልማትና ለማስተዋወቅ የጀመራቸው ጥረቶች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ጎንደር ከተማ በታሪካዊ ስራዎች ይበልጥ እየተገለጠች መሆኗን ገልጸው÷ ሁሉን አቀፍ ስራዎችን ከሕብረተሰቡ ጋር በመሆን ማስቀጠል እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ የዩኒቨርሲቲውን የ2018 ስድስት ወራት አፈፃፀምን የገመገመ ሲሆን÷ የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አክሊሉ ታደሰ (ዶ/ር) ተቋሙ በመማር ማስተማርና ምርምር ስራዎች የተሻለ ውጤት አስመዝግቧል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ያደረጋቸው ጥረቶች የሚበረታቱ መሆናቸውንና የውስጥ ገቢውን ለማሳደግ የጀመራቸውን ስራዎች ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።

የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስማማው ዘገየ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ተቋሙ በዋና ዋና ዘርፎች አበረታች ስራዎችን መከወን መቻሉን ጠቅሰው÷ የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክን ለማልማትና ለማስተዋወቅ ስራዎች መጀመሩን አመልክተዋል።

የቱሪዝም ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ከሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳደር ጋር በቅርበት እየተሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በምናለ አየነው

Exit mobile version