Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የዘመናዊቷ ቱርክዬ አርክቴክት በመባል የሚታወቁት ኤርዶዋን…

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከኢስታንቡል ከንቲባነት እስከ ሀገር መሪነት የተጓዙትና የዘመናዊቷ ቱርክዬ አርክቴክት በመባል የሚታወቁት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን።

በፈረንጆቹ 1954 በኢስታንቡል ከተማ የተወለዱት ኤርዶዋን የፖለቲካውን ዓለም የተቀላቀሉት በፈረንጆቹ 1994 የኢስታንቡል ከንቲባ በመሆን ነበር።

የከተማዋ ከንቲባ በነበሩበት ወቅት በውሃ አቅርቦት፣ በትራንስፖርት እና ሌሎች ችግሮችን በመቅረፍ እና ለውጥ ማምጣት በመቻላቸው ምክንያት በመላ ሀገሪቱ ተወዳጅ መሆን ችለዋል።

ከዚያም በፈረንጆቹ 2001 ከሌሎች ፖለቲከኞች ጋር በመሆን በኢኮኖሚ ልማት፣ በፖለቲካ መረጋጋትና በዴሞክራሲ ጉዳዮች ለውጥን ለማምጣት ዓላማ ያደረገውን የፍትህ እና የልማት ፓርቲ (ኤኬፒ) መመስረት ችለዋል፡፡

ፓርቲያቸው በ2002 የተካሄደውን የቱርክዬ አጠቃላይ ምርጫ ማሸነፉን ተከትሎ፥ በ2003 25ኛው የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ተሹመዋል፡፡

የቱርክዬ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣንን ከተረከቡ በኋላ ለኢኮኖሚና ለተቋማት ግንባታ ቅድሚያ በመስጠት ስራቸውን የጀመሩ ሲሆን፥ በዚህም በኢኮኖሚና በዘመናዊ መሠረተ ልማት ግንባታ ከፍተኛ እድገት እንዲመዘገብ አድርገዋል።

በዚህም ትላልቅ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች የአስተዳደራቸው ዋነኛ መገለጫ ሆነው መውጣት መጀመራቸው ይነገራል፡፡

ለትራንስፖርት ዘርፍ ከፍተኛ በጀት በመመደብ ግዙፍ ድልድዮችን ገንብተዋል፤ የፈጣን ባቡር መስመሮችን አስፋፍተዋል፤ እንዲሁም የኢስታንቡል አውሮፕላን ማረፊያን በዓለም ላይ ካሉት ትላልቅ የአቪዬሽን ማዕከላት አንዱ እንዲሆን አስችለዋል።

ለኢንዱስትሪና የመከላከያ ዘርፎች ስትራቴጂያዊ ትኩረት በመስጠት የቴክኖሎጂ ማዕከላትና የመከላከያ ኢንዱስትሪን ጨምሮ የኢንዱስትሪ ዘርፉ በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ ቁልፍ የመሪነት ሚና ተጫውተዋል።

በ2014 በተደረገው የቱርክዬ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በቀጥታ በህዝብ የተመረጡ የመጀመሪያው የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት መሆን የቻሉ ሲሆን፥ በ2017 ሀገሪቱን ከፓርላማ ወደ ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት የሚያሸጋግረው የሕገ መንግስት ማሻሻያ መጽደቁ የሚታወስ ነው።

በፕሬዚዳንትነት ግዜያቸው ቱርክዬ በዓለም አቀፉ የዲፕሎማሲ ማኅበረሰብ ዘንድ ያላት ተሰሚነት በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር አድርገዋል።

ኤርዶዋን በመሪነት ዘመናቸው ዕውን ካደረጓቸው ግዙፍ መሠረተ ልማቶች መካከል፡-

👉 የኢስታንቡል አውሮፕላን ማረፊያ፡ በየዓመቱ ከ200 ሚሊየን በላይ መንገደኞችን ማስተናገድ የሚችልና በዓለም ላይ ካሉ ትላልቅ የአውሮፕላን ማረፊያዎች አንዱ ነው።

👉 የማርሜራይ ዋሻ፡- በፈረንጆቹ 2013 የተከፈተው ይህ የባቡር ዋሻ ከ13 ኪሎ ሜትር በላይ የሚረዝም ሲሆን አውሮፓና የእስያ የሚያገናኝ በባሕር ስር የተገነባ ዋሻ ነው።

👉 1915 የቻናካል ድልድይ፡- የዓለም ላይ ረጅሙን ተንጠልጣይ ድልድይ ክብረወሰን የያዘ ሲሆን የአካባቢውን ኢንዱስትሪ ዞኖች የሚያገናኝ ቁልፍ ፕሮጀክት ነው።

👉 የፈጣን ባቡር መስመር ዝርጋታ፡ የሀገሪቱን ዋና ዋና ከተሞች የሚያገናኝ የፈጣን ባቡር መስመር ሲሆን በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ውህደትንና ዘመናዊ የትራንስፖርት እንቅስቃሴን ያጠናከረ ነው።

ኤርዶዋን በመሪነት ዘመናቸው በቱርክዬ እና አፍሪካ መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር ማድረግ የቻሉ ሲሆን፥ በአኅጉሪቱ በርካታ ኤምባሲዎች እንዲከፈቱ፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር እንዲጠናከር አድርገዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በብዙ የአፍሪካ ከተሞች መዳረሻዎቹን ማስፋት በቻለው የቱርክዬ አየር መንገድ አማካኝነት የንግድና የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲያድግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡

በተጨማሪም እንደ ትምህርት፣ ጤናና የሙያ ስልጠና ባሉ ዘርፎች ላይ የልማት ፕሮጀክቶችን ማስፋፋት ችለዋል፡፡

ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር እንዲጠናከር ከማድረጋቸው ባሻገር በወታደራዊ፣ በፋይናንስና ሌሎች አዳዲስ የትብብር ዘርፎች የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማሳደግ የበኩላቸውን እየተወጡ ይገኛሉ፡፡

ለረዥም ዓመታት የቱርክዬ የፖለቲካ ማዕከል የሆኑት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን በኢኮኖሚ፣ በመሠረተ ልማትና በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ሀገሪቱ የአሁኑን ቁመና እንድትይዝ ያስቻሉ መሪ ናቸው።

በዚህም በአርቆ አሳቢነት የሚደነቁት ፕሬዚዳንቱ በቱርክዬ በፈጠሩት ከፍተኛ ተጽዕኖ የዘመናዊቷ ቱርኪዬ አርክቴክት ለመባል በቅተዋል፡፡

በዮናስ ጌትነት

Exit mobile version