Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በምርጫ ወቅት አቤቱታዎች ሲቀርቡ በህግ አግባብ ፈጣን እልባት ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ነው – አቶ ቴዎድሮስ ምህረት

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አቤቱታዎች ሲቀርቡ በህግ አግባብ ብቻ ፈጣን እልባት ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ነው አሉ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት።

ፕሬዚዳንቱ ዝግጅቶች እየተደረጉ የሚገኙት በኢትዮጵያ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 እና በሥነ ሥርዓት ህጉ መሰረት መሆኑን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል።

በዚህም በአሁኑ ወቅት ከወረዳ ፍርድ ቤቶች ጀምሮ እስከ ሰበር ሰሚ ችሎት የውጭ ሀገራት ተሞክሮን በማጣመር ለዳኞች ስልጠና ለመስጠት አማካሪ መቀጠሩን አብራርተዋል።

ለዝግጅቱ በቅድሚያ በዘርፉ ላይ የዳሰሳ ጥናት መደረጉን ጠቅሰው÷ የፌደራል እና ክልል ዳኞችን ማዕከል በማድረግ ለተመረጡ ዳኞች በሦስት ዙር የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

በቅድመ ምርጫና ድህረ ምርጫ በፖለቲካ ፓርቲዎች ሊነሱ የሚችሉ አቤቱታዎች ህግን በመከተል የተፋጠነ እልባት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በመጪው ምርጫ ከፍተኛውን የሕዝብ ድምጽ የሚያገኝ የፖለቲካ ፓርቲ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሰላማዊ ሽግግር እንዲያደርግ በገለልተኝነት በሕግ አግባብ እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version