አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአውሮፓ እና እስያ አማካይ ስትራቴጂያዊ መገኘት ያላት ቱርክዬ ባለፉት የሩብ ክፍለ ዘመን ጊዜያት የተገበረቻቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች በዓለማችን 17ኛ ኢኮኖሚ ባለቤት ለመሆን አብቅተዋታል፡፡
በፈረንጆቹ 2001 ባስተናገደችው የኢኮኖሚና የፋይናንስ ቀውስ ከፍተኛ የዋጋ ንረት፣ የእዳ ጫና፣ ደካማ የባንክ ሥርዓት፣ የኢንቨስትመንት እና የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከምና መሰል ችግሮች ውስጥ ማለፏ ይነገራል፡፡
ከዚህ ቀውስ ለመውጣት የወሰደቻቸው ርምጃዎች ከቀውስ እንድትወጣ ከማስቻል ባለፈ ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት እንድታስመዘግብ መሰረት መጣል ችለዋል፡፡
በፈረንጆቹ 2003 25ኛው የቱርክዬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን የሚመሩት የፍትህና ልማት ፓርቲ (ኤኬፒ) በምርጫ አሸንፎ ቱርክዬን መምራት ሲጀምር የኢኮኖሚ ማሻሻያ ጅምሮችን ማጠናከር ላይ መጠመዱ ይታወሳል፡፡
በዚህም ሀገሪቱን ከኢኮኖሚ ውድቀት ለመታደግ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን በመደገፍ፣ የፋይናንስ ዘርፉን በማጠናከርና ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት ማክሮ ኢኮኖሚን ማረጋጋት ላይ ያተኮሩ ማሻሻያዎችን አድርጓል፡፡
በእነዚህና መሰል ማሻሻያዎች በመታገዝ የሰው ኃይልን፣ ቴክኖሎጂንና ካፒታልን በአግባቡ በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የቻለች ሲሆን፥ ይህም አሁን ላይ ለደረሰችበት የኢኮኖሚ እድገት መነሳሻ እንደሆናት የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
በዋናነት በአውቶሞቲቭ፣ ጨርቃጨርቅ፣ ማሽነሪና የኤሌክትሮኒክስ ኢንዱስትሪ ዘርፎች የምትታወቅ ሲሆን፥ የአገልግሎት ዘርፍ ሀገሪቱ ከፍተኛ ገቢ የምታገኝበት ዘርፍ ነው፡፡
ለአብነትም በአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ከአውሮፓ ቀዳሚ ሀገራት ተርታ የምትሰለፍ ሲሆን፥ በዓለማችን የመኪና ሽያጭ ባላት ድርሻ 13ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
ከ85 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ያላትና ለአውሮፓና እስያ አማካይ ስትራቴጂያዊ በሆነ አካባቢ የምትገኘው ቱርክዬ ከሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ መረጋጋት ባለፈ በዓለም ኢኮኖሚ ድርሻዋን ከፍ ማድረግ ችላለች፡፡
ቱርክ ከአፍሪካ ጋር ያላት የንግድ ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ እድገት ያሳየ ሲሆን፥ ለአብነትም በፈረንጆቹ 2024 ከአፍሪካ ሀገራት ጋር የ37 ቢሊየን ዶላር የንግድ ልውውጥ አድርጋለች፡፡
ከ500 ዓመታት የተሻገረ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ኢትዮጵያ እና ቱርክዬ በአሁኑ ወቅት ጠንካራ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር አላቸው፡፡
በኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንት በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ሀገራት አንዷ የሆነችው ቱርክዬ በተለይም በጨርቃጨርቅ፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግና በግብርና ግብዓት ዘርፎች እንዲሁም በዲጂታል መሰረተ ልማት ከፍተኛ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡
በኢትዮጵያ ከ260 በላይ የቱርክዬ ኩባንያዎች ከ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በላይ የሚገመት የኢንቨስትመንት ተሳትፎ የሚያደርጉ ሲሆን፥ በ10 ሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዋናነት ቡና እና ጥራጥሬዎችን ጨምሮ እንደ ሰሊጥና ተልባ ያሉ የቅባት እህሎችን ወደ ቱርክዬ የምትልክ ሲሆን፥ ለአብነትም በፈረንጆቹ 2024 ከ42 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር በላይ የሚገመት ምርት ወደ ቱርክዬ ልካለች።
በአንጻሩ ቱርክዬ ወደ ኢትዮጵያ ከምትልካቸው ምርቶች መካከል ለግንባታ ግብዓት የሚሆን ብረታብረት፣ መድሃኒትና የኢንዱስትሪ ግብዓቶች በዋናነት ይጠቀሳሉ።
ይህ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊ ግንኙነት ከማጠናከር ባለፈ ለስትራቴጂያዊ አጋርነታቸው መሸጋገሪያ ድልድይ የሚሆን ነው።
በኃይለማሪያም ተገኝ

