አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በ39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤና በ2ኛው የጣሊያን-አፍሪካ ጉባኤ ብሔራዊ ጥቅሞቿን ያስጠበቀ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት አግኝታለች አለ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ ባለፉት ቀናት በመዲናዋ የተካሄዱትን ሁለት ትልልቅ ጉባኤዎች አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው በመግለጫቸው እንዳሉት፥ ጉባኤዎቹ በስኬት መጠናቀቃቸው ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን የማስተናገድ አቅሟን ማሳደጓን የሚያመላክት ነው፡፡
ኢትዮጵያ ሁለቱን ጉባኤዎች ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ማስተናገዷን ጠቅሰው፥ እንግዶቿን በክብር ተቀብላ በክብር ሸኝታለች ነው ያሉት፡፡
በ39ኛው የኅብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ላይ 41 የሀገራት መሪዎች፣ 48 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ጨምሮ ከ20 ሺህ በላይ እንግዶች መሳተፋቸውን አመልክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሁለቱ ጉባኤዎች በዋናነት አራት ስኬቶችን አስመዝግባለች ያሉት አምባሳደሩ፥ እንግዶቿን በመቀበልና በመሸኘት በኩል ባህሏን ያስተዋወቀችበት ሁነት እንደነበር አንስተዋል፡፡
ከጉባኤዎቹ ጎን ለጎን ስኬታማ የባለብዙ ወገን መድረክ በማድረግ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ያስጠበቀ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ተገኝቷል ብለዋል፡፡
የተለያዩ የልማት ስራዎችን በማሳየት የገጽታ ግንባታ ስራዎች መሰረታቻውን ገልጸው፥ ጉባኤዎቹ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን የማስተናገድ አቅሟ ማደጉን ያመላከቱ ሁነቶች እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው በዚሁ ወቅት ጉባኤዎቹ በተሟላና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንዲካሄዱ ላደረጉ ሁሉም አካላት እንዲሁም ለመዲናዋ ነዋሪዎች ምስጋና አቅርበዋል።
በታሪኩ ለገሰ

