አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኢንዱስትሪዎች ይገጥሟቸው የነበሩ ችግሮችን በመፍታት የማምረት አቅማቸው እንዲጎለብት አድርጓል አሉ።
የኢትዮጵያን ምርቶች ማስተዋወቅ እና ተጨማሪ የገበያ ዕድሎችን የማስፋት ዓላማ ያነገበው 4ኛው ዙር ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የ2018 ኤክስፖ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
አቶ መላኩ አለበል በመርሐ ግብሩ ላይ እንዳሉት፤ ንቅናቄው የሀገር ውስጥ ምርት አጠቃቀም ላይ ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል።
ከዚህ ቀደም ኢንዱስትሪዎች ያጋጥሟቸው የነበሩ ችግሮችን በመፍታት ረገድ ንቅናቄው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸው፤ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ እንዲፈቱ በማድረግ የማምረት አቅማቸው እንዲጎለብት አድርጓል ብለዋል።
የዘንድሮ የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ‘ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት ለኢትዮጵያ ታምርት’ በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል ከሚያዝያ 24 እስከ 28 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።
በ4ኛው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ 270 አምራቾች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸው፤ የገበያ ትስስሮችን ለመፍጠርና የምርት ጥራትን ለማሻሻል ጉልህ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።
ከ2 ሺህ በላይ ጎብኚዎች የሚጠበቅበት ይህ ኤክስፖ ፈጠራን እንደሚያበረታታ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የልምድ ልውውጥ እንደሚደረግበት ተናግረዋል።
በኤክስፖው ላይ የፓናል ውይይቶች፣ የምርት ልማት ውድድሮች፣ የተሻለ አፈፃፀም ላላቸው ኢንዱስትሪዎች የዕውቅና ፕሮግራም እና ሌሎችም መርሐ ግብሮች እንደሚከናወን ተጠቁሟል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ታምርት የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ይካሄዳል።
በግዛቸው ግርማዬ

