አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ 39ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባዔ እንግዶችን በማስተናገድ ረገድ ኩራትን የሚፈጥሩ ተግባራት የተገለጡበት ነበር አሉ።
የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እና የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችውን አዲስ አበባ ለጉባዔው ጽዱ፣ ውብ እና ሰላማዊ እንዲሁም የአፍሪካዊያን ኩራት እንድትሆን የተለያዩ ባለድርሻዎች አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
ጉባዔው በስኬት እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን ለተወጡ አካላት የእውቅና እና ምስጋና መርሐ ግብር ተካሂዷል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ከተማችን በሰላማዊነትና በዘላቂ ልማቷ ምሳሌ ሆናለች ብለዋል።
ከተማዋ በሰላም ወጥተው የሚገቡባት፣ የቱሪስት መዳረሻ እና የበርካታ ኮንፈረንሶች ማዕከል በመሆን የቱሪዝም ዘርፍ እንዲያድግ እያገዘች መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም ባለመልማታቸው ያሳፍሩ የነበሩ የከተማዋ ገጽታዎች ተቀይረው ውበት መላበሳቸውን አንስተው፤ ባለፈው ሳምንት በተስተናገደው የአፍሪካ ህብረት ጉባዔ በውበት የተገለጠው የመዲናዋ መልክ ጎልቶ መታየቱን አንስተዋል።
ጉባዔው እንግዶችን በማስተናገድ በኩልም አዳዲስ ልምምዶች እና ኩራትን የሚፈጥሩ ተግባራት የተገለጡበት ነበር ብለዋል፡፡
ለጉባዔው ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱት የጸጥታ አካላት፣ የከተማዋ ተቋማት፣ ለቦሌ ብራስ ቪ አይ ፒ መንገድ ግንባታ እንዲሁም ለከተማዋ ነዋሪዎች ምስጋና አቅርበዋል።
በይስማው አደራው

