አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በወለጋ ዞኖች ያደረግነው ጉብኝት እጅግ በጣም ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ የታየበት ነው አሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ።
አቶ ጌታቸው ይህንን ያሉት በወለጋ ዞኖች በተደረገ የልማት ሥራዎች ጉብኝት ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያ ነው።
የተሰሩ የልማት ስራዎች ኢትዮጵያ ያላት የተፈጥሮ ጸጋ፣ ለመስራት ዝግጁ የሆነ አመራር፣ የአመራሩን መንገድ ተከትሎ አመራሩንም ጭምር ገፍቶ ወደ ልማትና ስራ መግባት የሚችል ሕዝብ እስካለ ድረስ ሀገሪቱን በአጭር ጊዜ መለወጥ እንደሚቻል የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
በወለጋ ዞኖች ያደረግነው ጉብኝት ብዙ ጊዜ ከልማት ጋር ሳይሆን ከጸጥታ ችግር ጋር ማያያዝ የተለመደውን አካባቢ ታሪክ የቀየረ ነው ብለዋል።
ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መንቀሳቀስ አስቸጋሪ ተደርጎ የሚሳልበት አካባቢ መጥተን እጅግ በጣም ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ተመልክተናል ነው ያሉት፡፡
ሕዝቡም የታየውን እንቅስቃሴ ማድነቅ ብቻ ሳይሆን የበለጠ ጎልቶ እንዲወጣና እንዲጠናከር ለማድረግ ሙሉ ቁርጠኝነት ያሳየበት ሆኖ እንዳገኙት አስረድተዋል፡፡
አካባቢው ብዙ ጊዜ ልማት ርቆባቸዋል ተብሎ ከሚነገሩና አንዳንዱ አፍራሽ መልዕክት ለማስተላለፍ በሚፈልግበት ሰዓት ሕግና ሥርዓት የሌለበት አካባቢ ተደርጎ የሚቆጠር እንደነበር አመልክተዋል።
በተግባር ግን ሕዝቡ ተፈጥሮ የለገሰውን ጸጋ በራሱ ጉልበትና በልጆቹ አመራር ጭምር አጠናክሮ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚንቀሳቀስበትና ትልቅ ተስፋ ያለበት አካባቢ ሆኖ ነው ያገኘሁት ሲሉም አውስተዋል፡፡
በአድማሱ አራጋው

