Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአቶ አማን ፍሰሐፂዮን የአስክሬን ሽኝት መርሐ ግብር እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢቢኤስ ቴሌቪዥን መስራች እና ባለቤት የአቶ አማን ፍሰሐፂዮን የአስክሬን ሽኝት መርሐ ግብር በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው፡፡
አቶ አማን ፍሰሐፂዮን ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው የካቲት 4 ቀን 2018 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን÷ አስክሬናቸው በትናንትናው ዕለት ከአሜሪካ ወደ አዲስ አበባ መጥቷል።
በአቶ አማን ፍሰሐፂዮን አስክሬን ሽኝት መርሐ ግብር ላይ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስጣንን ጨምሮ የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ተወካዮች፣ የሟች ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች እንዲሁም የሙያ ባልደረቦችና የሐይማኖት አባቶች ተገኝተው የአበባ ጉንጉን አኑረዋል።
በመድረኩ አቶ አማን ኢቢኤስ ቴሌቪዥንን በማቋቋም የመገናኛ ብዙኃን የብሮድካስት ዘርፍ እንዲነቃቃ በማድረግ አበርክቷቸው የጎላ እንደነበር ተገልጿል።
በተጨማሪም ሀገርን የሚጠቅሙ ሥራዎችን በመስራት እንዲሁም የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የቦርድ አባል በመሆን በትምህርት ዘርፍ ውስጥ አስተዋፅኦ እንደነበራቸው ተመላክቷል።
የአቶ አማን ፍሰሐፂዮን ሥርዓተ ቀብር በቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ መካነ መቃብር በዛሬው ዕለት የሚፈጸም ይሆናል።
በሚልኪያስ አዱኛ
Exit mobile version