አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ27ኛ ሳምንት መርሐ ግብር በዋንጫ ፉክክሩ ወሳኝነት ያላቸው ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይደረጋሉ፡፡
የሊጉ መሪ አርሰናል በተከታታይ ነጥብ መጣሉን ተከትሎ ወደ ዋንጫ ፉክክሩ ይበልጥ የተጠጋው ማንቼስተር ሲቲ ዛሬ ምሽት 5 ሰዓት በኢቲሃድ ስታዲየም ኒውካስል ዩናይትድን ያስተናግዳል፡፡
በ53 ነጥቦች በሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሲቲ የነጥብ ልዩነቱን ወደ ሁለት ለማጥበብ ወደ ሜዳ ይገባል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች፥ ማንቼስተር ሲቲ ሦስቱን ሲያሸንፍ በአንዱ አቻ ተለያይቶ በቀሪው አንድ ጨዋታ ሽንፈት አስተናግዷል፡፡
በሊጉ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ማሸነፍ የቻለው እንግዳው ቡድን ኒውካስል ዩናይትድ በሦስቱ ተሸንፎ በአንዱ አቻ ተለያይቷል፡፡
አርሰናል በተከታታይ ባባከናቸው ነጥቦች የዋንጫ ተስፋቸውን ያለመለሙት ማንቼስተር ሲቲዎች የዛሬ ምሽቱን ጨዋታ የሚያሸንፉ ከሆነ የዋንጫ ትንቅንቁ የሚያይል ይሆናል፡፡
በሌላ ጨዋታ ምሽት 12 ሰዓት ላይ የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ በሊጉ 19ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን በርንሌይ በስታምፎርድ ብሪጅ ያስተናግዳል፡፡
አስቶን ቪላ ከሊድስ ዩናይትድ፣ ብሬንትፎርድ ከብራይተን በተመሳሳይ ምሽት 12 ሰዓት የሚገናኙ ሲሆን፥ ምሽት 2 ሰዓት ከ30 ዌስትሃም ዩናይትድ ከቦርንማውዝ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
ፕሪሚየር ሊጉ ነገ ቀጥሎ ሲደረግ የሊጉ መሪ አርሰናል ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ከሜዳው ውጪ ቶተንሃም ሆትስፐርን የሚገጥምበት የሰሜን ለንደን ደርቢ ከወዲሁ ተጠባቂ ነው፡፡
በሳምንቱ አጋማሽ የ31ኛ ሳምንት መርሐ ግብራቸውን በሊጉ መጨረሻ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ዎልቭስ ጋር ያደረጉት መድፈኞቹ 2 ለ 2 አቻ መለያየታቸው ይታወሳል፡፡
ይህንን ጨዋታ ጨምሮ የፈረንጆቹ 2026 ከገባ ወዲህ ካደረጓቸው ስምንት የሊጉ ጨዋታዎች ሦስቱን ያሸነፉት መድፈኞቹ በአራቱ አቻ ተለያይተው በማንቼስተር ዩናይትድ ሽንፈት አስተናግደዋል፡፡
በዚህም መሰብሰብ ከነበረባቸው 24 ነጥቦች 13 ያህሉን ብቻ በማግኘት ከተከታዮቻቸው ማንቼስተር ሲቲ እና አስቶን ቪላ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ማስፋት የሚችሉባቸውን እድሎች ሳይጠቀሙ ቀርተዋል፡፡
ማንቼስተር ሲቲ በፈረንጆቹ 2026 ካደረጋቸው የመጀመሪያዎቹ አምስት የሊጉ ጨዋታዎች በሦስቱ አቻ ተለያይቶ በአንዱ ሽንፈት ያስተናገደ ሲሆን ማሸነፍ የቻለው አንዱን ብቻ ነበር፡፡
ሆኖም አርሰናል በተመሳሳይ ወቅት ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች በሁለቱ አቻ ተለያይቶ በአንዱ ሽንፈት ያስተናገደ ሲሆን፥ ከተከታዩ ማንቼስተር ሲቲ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ማስፋት የሚችልበትን እድል አባክኗል፡፡
መድፈኞቹ ይኸው 2026 ከገባ ወዲህ ከመምራት ተነስተው አቻ በመለያየትና በመሸነፍ ሰባት ነጥቦችን አጥተዋል፡፡
አሰልጣኝ ቶማስ ፍራንክን በማሰናበት የቀድሞውን የዩቬንቱስ እና ላዚዮ አሰልጣኝ ኢጎር ቱዶር እስከ ውድድር ዓመቱ መጨረሻ የሾሙት ስፐርሶች በነገው ጨዋታ ለሚኬል አርቴታው ቡድን ከባድ ተጋጣሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ነገ ቀን 11 ሰዓት ላይ ሊቨርፑል ወደ ሲቲ ግራውንድ አቅንቶ ከወራጅ ቀጣናው በሦስት ነጥብ ብቻ ከፍ ብሎ የሚገኘውን ኖቲንግሃም ፎረስት ይገጥማል፡፡
የቀድሞው የዎልቭስ አሰልጣኝ ቪቶር ፔሬራ በውድድር ዓመቱ ሦስት አሰልጣኞችን ያሰናበተውን ኖቲንግሃም ፎረስት እየመሩ የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታቸውን ነገ ያደርጋሉ፡፡
ሰንደርላንድ ከፉልሃም እንዲሁም ክሪስታል ፓላስ ከዎልቭስ በተመሳሳይ ቀን 11 ሰዓት የሚደረጉ የነገ ጨዋታዎች ናቸው፡፡
ማንቼስተር ዩናይትድ ወደ መርሲሳይድ አቅንቶ በሂል ዲኪንሰን ስታዲየም ኤቨርተንን የሚገጥምበት የ27ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ሰኞ ምሽት 5 ሰዓት ላይ ይደረጋል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ

