አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ27ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር በሰሜን ለንደን ደርቢ ቶተንሃም ሆትስፐር ከአርሰናል ዛሬ ምሽት የሚያደርጉት ፍልሚያ በጉጉት ይጠበቃል፡፡
ከ22 ዓመታት በኋላ የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ጥረት እያደረጉ የሚገኙት መድፈኞቹ ባለፉት 7 ጨዋታዎች ሁለቱን ብቻ ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን÷ የዋንጫ ጉዟቸው ዳግም እንቅፋት እንደገጠመው በርካቶች እያነሱ ይገኛሉ::
ከሊጉ የወራጅ ቀጠና ቡድን ዎልቭስ ባደረጉት ጨዋታ ከ 2 ለ 0 መሪነት አቻ መለያየታቸውን ተከትሎም በአሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ እና በቡድኑ ላይ ከፍተኛ ጫና በርክቷል፡፡
ባለፉት ዓመታት ከኋላ በመነሳት ዋንጫ ሲነጥቃቸው የነበረው ማንቼስተር ሲቲ ትናንት ምሽት ኒውካስል ዩናይትድን በማሸነፍ የነጥብ ልዩነቱን ወደ ሁለት አጥብቧል፡፡
በሊጉ 16ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙትና ላለመውረድ የሚጫወቱት ስፐርሶች የደርቢውን ጨዋታ ለማሸነፍ ወደ ሜዳ የሚገቡ ሲሆን÷ ለመድፈኞቹ ብርቱ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡
በሄዱበት ክለቦች ሁሉ መሻሻልን በማምጣት የሚታወቁት አዲሱ የቶተንሃም አሰልጣኝ ኢጎር ቱዶር የዛሬው ጨዋታ የመጀመሪያው ከባድ ፈተናቸው ይሆናል፡፡
በአርሰናል በኩል ባለፉት ጨዋታዎች በጉዳት ምክንያት ለቡድኑ አገልግሎት ያልሰጡት ካይ ሃቨርትዝ እና ማርቲን ኦዲጋርድ ለጨዋታው ብቁ እደሚሆኑ ተመላክቷል፡፡
ጨዋታው ምሽት 1 ሰዓት 30 በቶተንሃም ሆትስፐር ስታዲየም ይደረጋል፡፡
በሌሎች የሊጉ መርሐ ግብሮች በተመሳሳይ 11 ሰዓት ላይ ክሪስታል ፓላስ ከዎልቭስ፣ ኖቲንግሃም ፎረስት ከሊቨርፑል እንዲሁም ሰንደርላንድ ከፉልሃም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
በአቤል ነዋይ

