Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ብራዚላዊው የማንቼስተር ዩናይትድ ኮከብ ካስሚሮ…

አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በማንቼስተር ዩናይትድ ቤት ምርጥ ብቃታቸውን እያሳዩ ከሚገኙ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው ብራዚላዊው ተጫዋች ካስሚሮ፡፡

የእግር ኳስ ሕይወቱን በሀገሩ ክለብ ሳኦፖሎ የጀመረው ካስሚሮ የቡድኑን ሚዛን በመጠበቅ ችሎታው ይታወቃል፡፡

በወቅቱ በተከላካይ አማካይ ስፍራ ላይ ባሳየው ድንቅ እንቅስቃሴ የሪያል ማድሪድን ቀልብ የሳበ ሲሆን÷ በ2013 ሎስብላንኮቹን መቀላቀል ችሏል፡፡

ካስሚሮ ሪያል ማድሪድን ከተቀላቀለ በኋላ በዋናው ቡድን ውስጥ የመጫወት ዕድል ባለማግኘቱ በውሰት ለፖርቶ መሰጠቱ ይታወሳል፡፡

በፖርቶ ቆይታው ካስሚሮ አስደናቂ እንቅስቃሴ በማድረግ ቡድኑን በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ውድድር ለሩብ ፍፃሜ ማብቃቱ አይዘነጋም፡፡

ካስሚሮ በፖርቶ ባሳየው ምርጥ ብቃት ሪያል ማድሪድ በ2015 ተጫዋቹን ወደ ሳንቲያጎ ቤርናባው መልሶ አምጥቶታል፡፡

ካስሚሮ ወደ ክለቡ ከተመለሰ በኋላ ለሪያል ማድሪድ ስኬት ወሳኝ ሚና በመጫወት ዓለም ላይ ካሉ ምርጥ የተከላካይ አማካዮች አንዱ መሆን ችሏል፡፡

ብራዚላዊው ተጫዋች በሪያል ማድሪድ በነበረው ቆይታ አምስት የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ፣ የስፔን ላሊጋ፣ የዓለም ክለቦች፣ የኮፓ ዴል ሬይን ጨምሮ የተለያዩ ዋንጫዎችን አሳክቷል፡፡

በሪያል ማድሪድ ቤት በቆየባቸው ዓመታት ከክሮሺያዊው ሉካ ሞድሪች እና ከጀርመናዊው ቶኒ ክሩስ ጋር የነበረው ጥምረት አስደናቂ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በሦስቱ ተጫዋቾች አስገራሚ ጥምረት የሪያል ማድሪድ የመሀል ሜዳ ክፍል ለዓመታት አስፈሪ ሆኖ መቆየትም ችሏል፡፡

ካስሚሮ ሪያል ማድሪድን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲቀላቀል በቂ የመሰለፍ ዕድል ማግኘት ባይችልም በድጋሚ ቡድኑን ከተቀላቀለ በኋላ ግን የቡድኑ አይነኬ ተጫዋች ለመሆን በቅቷል፡፡

ካስሚሮ ለሪያል ማድሪድ በሁሉም ውድድር 336 ጨዋታዎችን አድርጎ 31 ግቦችን አስቆጥሮ 29 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል፡፡

በስፔኑ ክለብ ሪያል ማድሪድ በዋንጫ የታጀቡ ዓመታትን ካሳለፈ በኋላ በ2022 የእንግሊዙን ክለብ ማንቼስተር ዩናይትድን ተቀላቅሏል፡፡

ካስሚሮ ማንቼስተር ዩናይትድን ከተቀላቀለ በኋላ የካራቦ ካፕ እና የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫዎችን አሳክቷል፡፡

በዚህ ወቅት ለማንቼስተር ዩናይትድ አስፈላጊ እና ወሳኝ ከሆኑ የቡድኑ ተጫዋቾች መካከል ካስሚሮ አንዱ ነው፡፡

ማንቼስተር ዩናይትድ የካስሚሮን ግልጋሎት በማያገኝባቸው ጨዋታዎች በመከላከሉ እና የቡድኑን ሚዛን በማስጠበቅ ረገድ ሲቸገር ይስተዋላል፡፡

ካስሚሮ በሚሰልፍባቸው ጨዋታዎች የቡድኑን ሚዛን በመጠበቅ፣ ለተከላካዮች ሽፋን በመስጠት እና የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ በመሳተፍ ለማንቼስተር ዩናይትድ ትልቁን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡

ሀገሩን ከፈረንጆቹ 2011 ጀምሮ እያገለገለ የሚገኘው ካስሚሮ ለብራዚል ብሔራዊ ቡድን እስካሁን ባደረጋቸው 82 ጨዋታዎች 8 ግቦችን ያሳቆጠረ ሲሆን÷ በ2019 የኮፓ አሜሪካ ዋንጫ አሳክቷል፡፡

አሁን እያሳየ በሚገኘው ምርጥ እንቅስቃሴ ለ2026 የዓለም ዋንጫ ለብራዚል ብሔራዊ ቡድን እንደሚጠሩ በአሰልጣኝ ካርሎ አንቸሎቲ ዋስትና ካገኙ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው።

በሪያል ማድሪድ በዋንጫ የታጀቡ ስኬታማ ዓመታትን አሳልፎ በማንቼስተር ዩናይትድ ምርጥ ብቃቱን እያሳየ የሚገኘው ካስሚሮ በፈረንጆቹ 1992 በዛሬዋ ዕለት ነው የተወለደው፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

Exit mobile version