የብልፅግና ፓርቲ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ከየካቲት 12 እስከ 14 ቀን 2018 ዓ.ም ለተከታታይ ሦስት ቀናት በመዲናችን አዲስ አበባ ተካሂዶ በስኬት ተጠናቅቋል፡፡
ምክር ቤቱ በመደበኛ ስብሰባው ሰፊ ዝግጅት እየተደረገለት የቆየውና በአሁኑ ጊዜ ወደ ዋና እንቅስቃሴው እየገባ ያለውን 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ዋነኛ አጀንዳው አድርጎ መክሯል፡፡
ለዚህም በቀደመው 6ኛ ጠቅላላ ምርጫ ላይ ፓርቲያችን ለሕዝብ የገባውን ቃል እና ስኬቶቹን በመንደርደሪያነት በመቃኘት የ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ አጠቃላይ ዝግጅት በጥልቀት ገምግሟል፡፡
ብልፅግና ፓርቲ ከሀገራዊ ለውጡ መባቻ ጀምሮ ለሕዝብ ከገባው ቃል አንዱና ዋነኛው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታችን ላይ ይስተዋል የነበረውን ስብራት መጠገን ነበር፡፡
ይህ አጀንዳ ከቃል እስከ ተግባር፤ ከተግባር እስከ ልምምድ የሚዘልቅ ረጅም ጉዞን የሚያጠቃልል ሲሆን÷ ጉዞውን በአስተማማኝ ውጥን ለመጀመር በቁርጠኝነትና መስዋዕትነት የታጀቡ አያሌ የተግባር ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡
የዴሞክራሲያዊ ሥርአትን ከገነቡ የተግባር ሥራዎች መካከል በተቃርኖ የቆዩ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ሰላማዊ ትግል እንዲያደርጉ የማድረግ፣ የህግ ማዕቀፎችን የማሻሻል፣ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን የማጠናከር፣ የዴሞክራሲ ባህል የማጎልበት እና በመደመር ዕሳቤ የመንግሥት ኃላፊነቶችን በፍትሃዊነት የማጋራት ተጨባጭና አዳዲስ የፖለቲካ ባህሎችን መፍጠር ተችሏል፡፡
ብልፅግና ፓርቲ እነዚህ አዳዲስ ባህሎች እንዲጠናከሩና ተቋማዊ መሠረታቸው እንዲጸና ለማስቻል 7ኛ ጠቅላላ ምርጫውን እንደ መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም ካለፈው ዓመት ጀምሮ አያሌ የውስጠ ፓርቲ እና የመንግሥት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡
በዚህ መሠረት መንትያ ግቦች የተቀመጡ ሲሆን ÷ አንደኛውና ቀዳሚው ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሀዊ፣ አሳታፊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የማድረግ መንግሥታዊ ኃላፊነትን በብቃት መወጣት ነው፤ ሁለተኛው ግብ ደግሞ ፓርቲው በጠንካራ ተፎካካሪነት በመሳተፍ አሸናፊ ሆኖ መውጣት ነው፡፡
የመንትያ ግቦቹ የእስካሁን አፈጻጸም በግምገማ የታየ ሲሆን ግቦቹ በተያዘላቸው የስኬት ሀዲድ ላይ እንደሚገኙ ተረጋግጧል፡፡
ይህ ስኬት በየደረጃው በተሰራ ሥራ ማለትም በውስጠ ፓርቲ፣ በመንግሥታዊ ተቋማት ትብብር፣ በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅንጅት፣ በባለድርሻ አካላት አስተዋጽኦ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በሕዝብ የነቃ ተሳትፎ የመጣ ውጤት መሆኑም በተመሳሳይ ተገምግሟል፡፡
ይህም የእስካሁኑ ስኬት ቀጣይና የማይቀለበስ እንዲሆን አይነተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዳንድ ነጠላ ትርክት ያነገቡ እንዲሁም ምርጫው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምን እንጂ የእነሱን ጊዜያዊ ጥቅም ለመጠበቅ ቦታ የሌለው መሆኑን የተረዱ የቅርብና የሩቅ ቡድኖች ምርጫውን ለማስተጓጎል ከመሞከር አልቦዘኑም፡፡
ይህም ቢሆን ሊያጋጥሙ ከሚችሉ እክሎች አንዱ መሆኑ ከመጀመሪያው ጀምሮ የተተነበየ ነበር፤የእነዚህ ቡድኖችን ምኞት ለማክሸፍም በቂ ሥራ እየተሰራ ቆይቷል፡፡
በቀጣይነትም ምርጫው በተቀመጠለት ጊዜ እና የተያዘለትን ግብ በማሳካት እንዲጠናቀቅ ለአንዳፍታም ቢሆን ሳንዘናጋ ሥራችንን የምንሰራ ይሆናል፡፡
ሕጋዊና ሕዝባዊ መንግሥት የማጽናት ሒደት ከምርጫ ውጭ በሚደረጉ ማንኛውም እንቅስቃሴዎች በፍጹም የማይሳካ ብቻ ሳይሆን ለአንዴም የማይደናቀፍ መሆኑ ግልፅ መሆን አለበት፡፡
ለዚህም ፓርቲያችን በህሊና የመጥራት እና በተቋማት የመብቃት ሥራዎቹን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
ህዝባችን እና በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላትም ይህንን አጠናክረው እንዲቀጥሉም አስፈላጊ የቅንጅት ሥራዎች ይሰራሉ፡፡
እያንዳንዱ ዜጋም ጠቅላላ ምርጫው የዴሞክራሲ ሥርዓት የሚገነባበት እና ሕጋዊና ህዝባዊ መንግሥት የሚጸናበት ብቸኛውና ሁነኛ ብሔራዊ ፕሮጀክት መሆኑን በመረዳት ለዴሞክራሲያዊነቱ፣ አሳታፊነቱ፣ ፍትሀዊነቱ፣ ሰላማዊነቱ እና ለአጠቃላይ ስኬቱ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
ብልፅግና ፓርቲ
የካቲት 16 ቀን 2018 ዓ.ም

