አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በኮሪደር ልማት የከተሞቻችንን ገጽታ ብቻ ሳይሆን የሥራ ባህላችን በመሰረታዊነት ተለውጧል አሉ።
የሚኒስቴሩ የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት አፈጻጸም የሴክተር ጉባዔ የተቋሙ አመራሮች፣ ሰራተኞች፣ ተጠሪ ተቋማት እና ሌሎች ባለድርሻዎች በተገኙበት እየተካሄደ ይገኛል።
ሚኒስትሯ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት÷ የኮሪደር ልማት ከተሞቻችንን በመቅረጽ ረገድ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
የኮሪደር ልማት ከመሰረተ ልማት ባሻገር ብዙ ጉዳዮችን አቅፎ መያዙን ገልጸው÷ በልማቱ የመንግሥት እሳቤዎችን፣ የልማት አካታችነትን፣ የህልም ግዝፈትን እና የሥራ ጥራትን ማሳየት መቻሉን አብራርተዋል።
በኮሪደር ልማት ከተሞቻችን ገጽታ ብቻ ሳይሆን የሥራ ባህላችን በመሰረታዊነት ተለውጧል ያሉት ሚኒስትሯ÷ በልማቱ ሌሎች ስለኛ ያላቸው አመለካከት ተቀይሯል ብለዋል።
ለከተሞች ብቻ ሳይሆን ለዘርፉ ጭምር በርካታ እድሎችን ይዞ የመጣው ኮሪደር ልማት የመፈጸም አቅማችንን አሳድጓልም ነው ያሉት።
በከተሞች እየተመዘገበ ያለው የኮሪደር ልማት ስኬት በገጠር መቀጠሉን አንስተው÷ የሀገራችንን የብልጽግና አይቀሬነት በሥራችን እናረጋግጣለን ብለዋል።
የሚሰራው የመንገድ እና የኮሪደር ልማት የበለጠ ትስስር፣ የበለፀገና ፍትሃዊ ሀገር የመመስረት ራዕይ እየተሳካ ስለመሆኑ ማሳያ እንደሆነም አመልክተዋል።
በቤዛዊት ከበደ

