አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2018 በጀት ዓመት ባለፉት ሰባት ወራት ከጋራ ገቢዎች ክፍፍል 71 ነጥብ 33 ቢሊየን ብር ለክልሎች ተላልፏል አሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፡፡
በገቢዎች ሚኒስቴርና በማዕድን ሚኒስቴር እየተተገበረ ያለውን የጋራ ገቢዎች አሰባሰብ፣ አስተዳደርና ትልልፍ ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ባደረገው የፋይናንስ ኦዲት ሪፖርት ግኝቶች ዙሪያ የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡
አቶ አገኘሁ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የጋራ ገቢዎች ክፍፍል ቀመር ማሻሻያን ተከትሎ የክልሎች የድርሻ ክፍፍል ከ4 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ወደ 91 ነጥብ 73 ቢሊየን ብር ከፍ ብሏል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ባካሄደው ተቋማዊ ሪፎርም የጋራ ገቢዎች ቀመርን ማሻሻያ በማድረጉ የክልሎች የጋራ ገቢዎች ድርሻ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
በማሻሻያው ወዲህ በ2017 በጀት ዓመት ለክልሎች 91 ነጥብ 73 ቢሊየን ብር ከጋራ ገቢዎች መተላለፉን አስታውሰዋል፡፡
በዚህ በጀት ዓመት ባለፉት ሰባት ወራት ደግሞ 71 ነጥብ 33 ቢሊየን ብር ለክልሎች ተላልፏል ነው ያሉት፡፡
የፌዴራልና የክልሎች የጋራ ገቢዎች አካል የሆነው ከከፍተኛ ማዕድንና ፔትሮሊየም ሀብቶች ልማት የሚሰበሰቡ የሮያሊቲ ገቢዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሻሻያ እያሳየ መጥቷል ብለዋል፡፡
በመድረኩ የክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮችን ጨምሮ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች መገኘታቸውን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽ/ቤት የኮሙኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ተረፈ በዳዳ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።

