አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በክልሉ እውቅና ያገኙ ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን ስራ ለማስጀመር የማደራጀት ስራ እየተሰራ ነው አለ።
በፍርድ ቤቱ የባህል ፍርድ ቤቶች አማካሪ ምክር ቤት ጽ/ቤት ሃላፊ ይማም ሰይድ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ባህላዊ ፍርድ ቤቶች የህግ አካላትን የስራ ጫና በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ አላቸው፡፡
ባህላዊ ፍርድ ቤቶች በማህበረሰቡ ዘንድ ያሉ ግጭቶችን በሽማግሌዎች አማካኝነት በእርቅ እና በማካካሻ መርህ በመፍታት ዘላቂ ሰላምንና ማኅበራዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ ሀገር በቀል ተቋማት መሆናቸውን አብራርተዋል።
በክልሉ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓቶችን በመለየትና ጥናት በማድረግ 15 የሚሆኑ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች በህግ እውቅና ማግኘታቸውን ገልጸው የተቀሩት ስርዓቶችም እውቅና እንዲያገኙ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
እውቅና ባገኙት ባህላዊ ፍርድ ቤቶች የፍርድ ስርዓቱን የሚመሩ ሽማግሌዎችን በክልሉ በሚገኙ 4 ሺህ 207 ቀበሌዎች የመምረጥ እና የማደራጀት ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የዳኝነት ስርዓቱን የሚመሩት ሽማግሌዎች ቋሚ ከሆኑ እንዲሁም ለአንድ ጉዳይ ብቻ የሚሰባሰቡ እና ቋሚ ያልሆኑ ሽማግሌዎች ከሆኑ ደግሞ ማህበረሰቡ በራሱ እንዲመርጥ እና ቋሚ ሽማግሌዎች እንዲኖሩ በማድረግ ምዝገባው እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ተደራሽ እና ወጪ ቆጣቢ ስርዓት መሆናቸውን ጠቁመው ባህልን ከማስቀጠል አንጻር የሚኖራቸው ፋይዳ የጎላ በመሆኑ ለባህላዊ የዳኝነት ስርዓቶች ህጋዊ እውቅና መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ከዚህ በፊት ማህበረሰቡ በሽምግልና ስርዓት መዳኘት ከጀመረ በኋላ የሽምግልና ሂደቱን ያቋርጥ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
አሁን ማህበረሰቡ በባህላዊ ስርዓት መዳኘትን ከመረጠ የፍርድ ሂደቱን እስከመጨረሻው መከታተል እና የሽማግሌዎቹን ውሳኔ የመቀበል ግዴታ አለበት ነው ያሉት።
በሶስና አለማየሁ

