አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት እና ሥራ ፕሮጀክት ዜጎችን ወደ ምርታማነት አሸጋግሯል አለ።
ሚኒስቴሩ የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት እና ሥራ ፕሮጀክት አፈፃፀም ግምገማ መድረክ እያካሄደ ይገኛል።
የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ፈንታ ደጀን በመድረኩ እንዳስታወሱት፤ ፕሮጀክቱ ከ10 ዓመት በፊት በ11 ከተሞች ጀምሮ በአሁኑ ወቅት በ88 ከተሞች እየተተገበረ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች በላይ ተጠቃሚ እያደረገ ነው።
ባለፈው ታሕሣሥ ወር 388 ሺህ ዜጎች በፕሮጀክቱ የነበራቸውን የቆይታ ጊዜ አጠናቅቀው ተመርቀው ሽግግር ማድረጋቸውንም አንስተዋል።
የተደረገውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ በመደኛው በጀት ከ879 ሺህ በላይ ዜጎች አስፈላጊ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንም አስረድተዋል።
መንግሥት እና የዓለም ባንክ በደረሱት ስምምነት ለዘርፋ የ250 ሚሊየን ዶላር የፋይናንስ ድጋፍ መገኘቱን ጠቅሰው፤ በዚህም በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት 318 ሺህ ዜጎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በከተሞች የሚከናወነውን የጽዳት፣ የአረንጓዴ ልማት፣ የተፋሰስ ልማት እና የአነስተኛ መሠረተ ልማት ሥራዎችን በማገዝ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል ነው ያሉት።
በ2017 በጀት ዓመት ብቻ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሁሉንም ድጋፍ አግኝተው ከፕሮጀክቱ ተመርቀው ከተረጂነት ወደ አምራችነት መሸጋገራቸውን ጠቅሰዋል።
በቤዛዊት ከበደ

