Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአማራ ክልል የአዳሪ ትምህርት ቤቶችን ግንባታ በዚህ ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በክልሉ የተጀመሩ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ግንባታ በዚህ ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው አለ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ መኳንንት አደመ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት፥ በክልሉ በ4 ቢሊየን ብር ወጪ ሦስት አዳሪ ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ ይገኛሉ፡፡
ትምህርት ቤቶቹ እየተገነቡ የሚገኙት በሰቆጣ፣ ደብረታቦር እና ፍኖተሰላም ከተሞች ሲሆን፥ ግንባታቸውን በዚህ ዓመት ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ትምህርት ቤቶቹ በሚቀጥለው የትምህርት ዘመን ለአገልግሎት ክፍት ይሆናሉ ነው ያሉት፡፡
በክልሉ ደሴ፣ ደብረማርቆስ እና ደብረብርሃን ከተሞች የሚገኙ አዳሪ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎችን ውጤት በማሻሻል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ በጎንደር ከተማ አስተዳደር ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር የአዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ ለማስጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡
ግንባታው በምዕራፍ ተከፍሎ የሚከናወን ሲሆን፥ ለዚህ ዓመት 272 ሚሊየን ብር መመደቡን የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ አስታውቋል፡፡
በምናለ አየነው
Exit mobile version