Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ስርዓትን የሚያዘምን ዲጂታል አሰራር ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ስርዓትን የሚያዘምን ዲጂታል አሰራር ይፋ አድርጓል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በማስተዋወቂያ መድረኩ ላይ እንዳሉት÷ የዲጂታል ስርዓቱ በኢትዮጵያ በእያንዳንዱ ወረዳ ምን አይነት የጤና ችግር አለ የሚለውን ለመለየት ያስችላል።

ስርዓቱ በፊት የነበረውን የተበታተነ የመረጃ አያያዝ የሚያስቀር መሆኑን ገልጸው÷ ይህም በየደረጃው የጤና መረጃ ልውውጥ እንዲሳለጥ ያግዛል ብለዋል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብጤ በበኩላቸው÷ ዲጂታል ስርዓቱ የጤና አደጋዎችን በተቀናጀ መልኩ ለመቆጣጠር እንደሚያግዝ አንስተዋል።

ተቋሙ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው÷ ዲጂታል ስርዓቱ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ርምጃዎችን ለመውሰድና የተቀናጀ የክትትል ስራ ለመስራት እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።

ዲጂታል ስርዓቱ ትንተናዎችን ለመስራት፣ ጊዜ ለመቆጠብና የታካሚዎችን መረጃ በአግባቡ ለማስቀመጥ ይረዳልም ነው ያሉት፡፡

በመርሐ ግብሩ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን÷ በአዲስ መልክ የተደራጀው የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ማስተባበሪያ ማዕከል ተመርቋል።

እንዲሁም ኢንስቲትዩቱ የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር  ስርዓትን ለማጠናከር የሚውሉ የመረጃና ግንኙነት ቴክኖሎጂ ግብዓቶችን አስረክቧል።

በየሻምበል ምህረት

Exit mobile version