Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በጋርዲዮላ ለምን እንደተፈለገ እያሳየ የሚገኘው ዶናሩማ…

አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለማንቼስተር ሲቲ የዋንጫ ፉክክር ትልቁን አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ ምርጥ ግብ ጠባቂ ነው ጂያንሉጂ ዶናሩማ፡፡

ጣሊያናዊው ግብ ጠባቂ ዶናሩማ ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ሕይወቱን የጀመረው በሀገሩ ክለብ ኤሲ ሚላን ነው፡፡

በጣሊያን ሴሪ አ የመጀመሪያ ጨዋታውን በ16 ዓመት ከ242 ቀናት ዕድሜው ያደረገ ሲሆን፥ በወቅቱ ሁለተኛው በዕድሜ ትንሹ ግብ ጠባቂ መሆን ችሎ ነበር።

ኤሲ ሚላን በ2020/21 የውድድር ዓመት በጣሊያን ሴሪ አ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ እንዲያጠናቅቅና በዚያው የውድድር ዘመን ከስምንት ዓመታት በኋላ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎ ቦታ እንዲያገኝ ዶናሩማ ትልቁን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡

ዶናሩማ በሚላን ቆይታው የጣሊያን ሴሪ አ የዓመቱ ምርጥ ግብ ጠባቂ ሽልማትን ማሸነፍ ችሏል፡፡

በጣሊያኑ ክለብ ኤሲ ሚላን ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ የቻለው ዶናሩማ ከስድስት ዓመታት የሚላን ቆይታ በኋላ በ2021 በነፃ ዝውውር የፈረንሳዩን ክለብ ፒኤስጂ ተቀላቅሏል፡፡

ዶናሩማ በፈረንሳዩ ክለብ ፒኤስጂ ቆይታው የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግን ጨምሮ የተለያዩ ዋንጫዎችን አሳክቷል፡፡

በተለይም በ2024/25 የውድድር ዓመት ፒኤስጂ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ ሲያሳካ የዶናሩማ ሚና ጉልህ እንደነበር ይታወሳል፡፡

የያሲን ትሮፊ ሽልማትን ሁለት ጊዜ ማሸነፍ የቻለው ዶናሩማ በ2025 የፊፋ የዓመቱ ምርጥ ግብ ጠባቂ ተብሎ መመረጥ ችሏል፡፡

በ2025 የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የዓመቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ መካተት የቻለ ሲሆን፥ የተለያዩ የግል ሽልማቶችን አሳክቷል፡፡

ጂያንሉጂ ዶናሩማ ሀገሩን ከ2016 ጀምሮ እያገለገለ ሲሆን፥ እስካሁን ድረስ ለጣሊያን ብሔራዊ ቡድን 79 ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡

ዶናሩማ በ17 ዓመት ከ189 ቀን ዕድሜው ለጣሊያን ብሔራዊ ቡድን በመጫወት በጣሊያን ብሔራዊ ቡድን ታሪክ በትንሽ ዕድሜ የተጫወተ ግብ ጠባቂ በመሆን ክብረ ወሰኑን ይዟል፡፡

ጣሊያን በፈረንጆቹ 2020 የዩሮ ዋንጫ ስታሳካ የስብስቡ አካል የነበረው ዶናሩማ ብሔራዊ ቡድኑ ውድድሩን እንዲያሸንፍ ትልቁን አስተዋጽኦ ማበርከቱ አይዘነጋም፡፡

ዶናሩማ በዩሮ 2020 የውድድሩ ምርጥ ተጫዋች እና ምርጥ ግብ ጠባቂ ሽልማትን ማሸነፉ ይታወሳል፡፡

በፈረንሳዩ ክለብ ፒኤስጂ በዋንጫ የታጀቡ ጊዜያትን ካሳለፈ በኋላ ባለፈው ክረምት ማንቼስተር ሲቲን ተቀላቅሏል፡፡

ዶናሩማ ማንቼስተር ሲቲን ከተቀላቀለ ወዲህ በዚህ የውድድር ዓመቱ ጥሩ ጊዜን እያሳለፈ ነው፡፡

በአሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ የሚመራው ማንቼስተር ሲቲ በሚወዳደርባቸው ውድድሮች ሁሉ ዋንጫውን ለማሳካት በሚያደርገው ጉዞ ውስጥ ዶናሩማ ትልቁን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡

በዚህ ወቅት እየተጫወቱ ከሚገኙ ምርጥ ግብ ጠባቂዎች መካከል አንዱ የሆነው ዶናሩማ በፈረንጆቹ 1999 በዛሬዋ ዕለት ነው የተወለደው፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

Exit mobile version